ነሀሴ 21 2017 - ''ኢትዮጵያ ውስጥ 25 የጂኦ ፓርክ ስፍራዎች መኖራቸውን ደርሼበታለሁ'' የቱሪዝም ሚኒስቴር
- sheger1021fm
- Aug 27
- 1 min read
የቱሪዝም ሚኒስቴር አደረግሁት ባለው ዳሰሳዊ ጥናት ኢትዮጵያ ውስጥ 25 የጂኦ ፓርክ ስፍራዎች መኖራቸውን ደርሼበታለሁ አለ፡፡
ባለፉት 10 ዓመት ውስጥ 229 የሚሆኑ ጂኦ ፓርኮች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (UNESCO) የተመዘገበ ሲሆን አፍሪካ እስካሁን 2 ብቻ በስሟ አስመዝግባለች፡፡
ጌታነህ አዲስ(ዶ/ር) በቱሪዝም ሚኒስቴር የፖሊሲ ተንታኝ (አናሊስት) ናቸው፡፡
ዩኔስኮ በአለም ላይ ያሉ የጂኦሎጂ ስፍራዎች ጠቀሜታን ባሉት መስፈርቶች በመመዘን አለም አቀፍ ቅርስ አድርጎ ይመዘግባቸዋል ያሉ ሲሆን የተደረገው ዳሰሳዊ ጥናት ኢትዮጵያ በዘርፉ ለአለም ቅርስነት የምታበረክተው ሃብት እንዳሏት አሳይቷል ብለዋል፡፡
እስካሁን ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሀብቱ ቢኖራቸውም በተገቢው መንገድ በዩኔስኮ ያላስመዘገቡበት ምክንያት ስለዘርፉ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑና በቂ ባለሞያ ስለሌላቸው ነበር ይላሉ፡፡
የቱሪዝም ሚኒስቴር ዳሰሳዊ ጥናት አድርጎ ካገኛቸው 25 ጂኦ ፓርክ ስፍራዎች መካከል 4ቱን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የሰነድ ማዘጋጀት ስራ ተጀምሯል ያሉን ጌታነህ አዲስ(ዶ/ር)፤ የሁለቱ ጂኦ ፓርክ ስፍራዎች መረጃ እስከ ህዳር 2018 ድረስ አጠናቅቆ ለዩኔስኮ ለመላክ ታቅዷል፡፡
ጌታነህ አዲስ(ዶ/ር) እንዳሉን አንድ ጂኦ ፓርክ በዩኔስኮ ለመመዝገብ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው መስፈርቶች መካከል አንዱ በአካባቢው ያለው ማህበረሰብ ከዘርፉ እንዴት ተጠቃሚ ይሆናል፣ በአካባቢው የሚኖረው ማህበረሰብ በምን መንገድ ይጠብቀዋል? የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡
ማህበረሰቡ ተጠቃሚ ያላደረገ ጂኦ ፓርክ እውቅና አይሰጠውም ከሌሎች ዩኔስኮ ከሚመዘግባቸው የቅርስ ዓይነቶች ይህ ባህሪው ልዩ ያደርገዋል በማለት ያስረዳሉ፡፡
ዩኔስኮ በየ4 ዓመቱ በጂኦ ፓርክነት የመዘገባቸው ስፍራዎች ክትትል ያደርግባቸዋል ያሉን በቱሪዝም ሚኒስቴር የፖሊሲ ተንታኝ የሆኑት ጌታነህ አዲስ (ዶ/ር) የሰጠውን ፈቃድ የሚያድሰውም ከዛ በኋላ ነው ብለዋል፡፡
በጂኦ ፓርኮች ውስጥ መሰረተ ልማት ሟሟላት አንዱና ዋንኛ መስፈርት ነው መንግስት ለዚህ ሚሆን ዝግጅት ከወዲሁ እያደረገ መሆኑንም ነግረውናል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስቴር ብሄራዊ ጂኦ ፓርኮችን ለማቋቋም እቅድ ይዟል፡፡
ይህ እውን ሲሆን በየዓመቱ በዩኔስኮ ጂኦ ፓርኮችን ለማስመዝገብ የቱሪዝም ሚኒስቴር ስራ እንደሚያቀልለት ጠቅሰዋል፡፡
በረከት አካሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments