top of page

ነሀሴ 20 2017 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Aug 26
  • 2 min read

የሶሪያ መንግስት የእስራኤል ጦር በደማስቆ አቅራቢያ ጥቃት አድርሶብኛል ሲል ከሰሰ፡፡


የእስራኤልን ጦር ድርጊት ወረራ ሲል የጠራው የሶሪያ መንግስት የፀጥታው ምክር ቤት ይፍረደኝ ማለቱን አናዶሉ ፅፏል፡፡


በከባድ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች የሚደገፉ የእስራኤል ወታደሮች በመዲናዋ ደማስቆ አቅራቢያ ወዳለችው ቤት ጂን ከተማ ዘልቀው ነበር ተብሏል፡፡

ree

የሶሪያ መንግስት የእስራኤል ጦር ድርጊት ለቀጠናው ሰላም በእጅጉ ያሰጋል ማለቱ ተሰምቷል፡፡


የፀጥታው ምክር ቤት አፋጣኝ እና ሁነኛ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል የሶሪያ መንግስት፡፡


በሶሪያ ከመንፈቅ በፊት ስልጣን የጨበጠው አዲሱ አስተዳደር በእስራኤል ላይ የጋረጥኩት አንድም የደህንነት ስጋት የለም ማለቱን መረጃው አስታውሷል፡፡


የሶሪያ መንግስት ወረራ እየተፈፀመብኝ ነው ስለማለቱ ከእስራኤል መንግስት በኩል የተሰማ አስተያየት የለም፡፡



የእስራኤል ጦር በጋዛ ደቡባዊ ክፍል በሚገኝ ሆስፒታል ላይ በፈፀመው የሚሳየል ድብደባ በጥቂቱ 20 ሰዎች ተገደሉ ተባለ፡፡


በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል አምስቱ የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ወኪሎች እንደሆኑ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


በእስራኤል ጦር የሆስፒታል ድብደባ የተገደሉት ለሬውተርስ ፣ ለአሶሼትድ ፕሬስ ፣ ለአልጀዚራ እና ለሚድል ኢስት አይ የሚሰሩ ጋዜጠኞች ነበሩ ተብሏል፡፡


ድብደባው በአለም አቀፍ ደረጃ እየተወገዘ መሆኑ ተሰምቷል፡፡


በዚሁ ድብደባ ከ5 ያላነሱ የጤና ባለሙያዎችም መገደላቸው ተጠቅሷል፡፡


የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ድብደባው የተፈፀመው በስህተት እንደሆነ ተናግረዋል ተብሏል፡፡



በሴኔጋል ለመጀመሪያ ጊዜ በM ፖክስ በሽታ የተያዘ ሰው ተገኘ፡፡


ግለሰቡ ባለፈው ሳምንት ከሌላ አገር ወደ ሴኔጋል የመጣ ነው መባሉን CNBC ፅፏል፡፡


በሴኔጋል ተገንቷል የተባለው የM ፖክስ ታማሚ ዜግነቱም ሆነ የመጣበት አገር በዘገባው አልተጠቀሰም፡፡


ግለሰቡ በአሁኑ ወቅትም በለይቶ ማቆያ ይገኛል ተብሏል፡፡


ከግለሰቡ ጋር ቅርበት ነበራቸው በተባሉ 25 ሰዎች ላይ የቅርብ ክትትል እየተደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡


የአለም የጤና ድርጅት M ፖክስን አለም አቀፋዊ የጤና ስጋት እንደሆነ ያወጀው ባለፈው አመት ነው፡፡


በሽታው በአሁኑ ወቅት በብዙ የአፍሪካ አገሮች በመስፋፋት ላይ እንደሚገኝ መረጃው አስታውሷል፡፡



በቻድ በመዛመት ላይ የሚገኘው የኮሌራ ወረርሽኝ 63 ሰዎችን ገደለ ተባለ፡፡


ወረርሽኙ በምስራቃዊቱ ኩአዳይ ግዛት እንደበረታ አናዶሉ ፅፏል፡፡


940 ያህል ሰዎች በኮሌራ መያዛቸው በምርመራ ጭምር ተረጋግጧል ተብሏል፡፡


ከመካከላቸውም የ63ቱ ሕይወት ማለፉን የጤና ሹሞች ተናግረዋል፡፡


ኮሌራ በንፅህና ጉድለት እና በተበከለ ውሃ ምክንያት የሚከሰት በሽታ ነው፡፡


እንደ ኮንጎ ኪንሻሣ ፣ ኮንጎ ብራዛቪል ፣ ጋና ፣ ኮትዲቭዋር፣ ናይጀሪያ ፣ ሱዳን እና ቶጎ ባሉ የአፍሪካ አገሮችም ኮሌራ መከሰቱን መረጃው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page