ነሀሴ 20 2017 - ''አፍሪካ ውስጥ ያለው የትምህርት ምዘና ሥርዓት ወጥ ለማድረግ የሚያስችል ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው'' የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት
- sheger1021fm
- Aug 26
- 1 min read
አፍሪካ ውስጥ ያለው የትምህርት ምዘና ሥርዓት ወጥ ከተደረገ ሰዎች ወደ የትኛውም የአህጉሪቱ ክፍል ሄደው የጀመሩትን ትምህርት እንዲቀጥሉ ይረዳል ሲል የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ተናገረ፡፡
የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት እንዳለው አሁን ባለው የምዘና ሥርዓት አንድ ተማሪ ከኢትዮጵያ ወጥቶ በሌሎች የአፍሪካ ሀገር ትምህርቱን ካቆመበት ለመቀጠል ይቸገራል፡፡
የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ(ዶ/ር) አፍሪካ ውስጥ ያለው የትምህርት ምዘና ሥርዓት ወጥ ለማድረግ የሚያስችል ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
ይህ ማዕቀፍ ለመተግበር እንዲቻል እየተደረገ ባለው የአፍሪካ የትምህርት ምዘና ጉባኤ ምክክር ይደረግበታል ያሉ ሲሆን ተሳታፊ ሀገራትም በአፍሪካ ህብረት በኩል ሀገራቸው ውስጥ እንዲተገበር ለማድረግ ቃል የሚገቡበት ነው ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ጨምሮ በሌሎች የአለም ሀገራት በምዘና ሥርዓት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች የፈተና ስርቆት፣ ምዘናዎች ደረጃቸውን ጠብቀው አለመዘጋጀት እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው ይላሉ ዶክተር እሸቱ፡፡
የትምህርት ምዘና የሚደረገው አንድ ተማሪ ምን ያህል አውቋል? የሚለውን ለመገንዘብና ተማሪው ያለበት ክፍተቶችን እንዲገነዘብ ለማድረግ ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ጨምሮ በሌሎች ሀገራት ያለው ግንዛቤ ግን ምዘና ሲባል የመውደቅና የማለፍ ብቻ ተደርጎ ይታያል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው 41ኛው የአፍሪካ የትምህርት ምዘና ጉባኤ እስከ አርብ ድረስ የሚቀጥል ሲሆን 30 የአፍሪካ ሀገራት በጉባኤው እየተሳተፉ ነው፡፡
በረከት አካሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s








