ነሀሴ 20 2017 - በአዲስ አበባ የሚገኙ ከሚገኙ 75 የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ዝቅተኛ መስፈርቱን አሟልተው የተገኙት 3ቱ ብቻ ናቸው ተባለ።
- sheger1021fm
- 3 hours ago
- 2 min read
በአዲስ አበባ የሚገኙ ሁሉም የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በአዲሱ መመዘኛ መሰረት ተገምግመው ዝቅተኛውን መስፈርት ያሟላ አንድም ተቋም ባለመገኘቱ፤ ከመመሪያው 485 መመዘኛዎች እንዲቀነሱ ተደርጓል ተባለ።
የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን፤ ተቋማቱ በመመሪያው ከተቀመጡ መመዘኛዎች ዝቅተኛ የሚባሉትን እንኳ የሚያሟሉ ተቋማት ስላላገኘሁ መመሪያው ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን እየቀነስኩ ለ3ኛ ጊዜ ለማሻሻል ተገድጃለሁ ብሏል።
ይህም ሆኖ በአዲስ አበባ ከሚገኙ 75 የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ዝቅተኛ መስፈርቱን አሟልተው የተገኙት 3ቱ ብቻ ናቸው ተብሏል።
በዚህ ውጤት መሰረት ውሳኔ ከተሰጠ፤ ውጤቱ የከፋ ስለሚሆን ያላሟሉት መስፈርቶች በጊዜ ገደብ እንዲያሟሉ እድል እንደተሰጣቸው ተነግሯል።
ከመጀመሪያው መመሪያ ከተቀነሱት 485 መስፈርቶች በተጨማሪ በጊዜ ገደብ እንዲያሟሉ በሚል የተቀነሱላቸው መስፈርቶችም በርካታ ናቸው ተብሏል።
ለ3ኛ ዙር በተከለሰው መመሪያ መሰረትም 3 የትምህርት ተቋማት፣ 3 ካምፓሶች እና 17 ፕሮግራሞች(የትምህርት መስኮች) ብቻ ዝቅተኛ የተባለውን መስፈርት አሟልተው ተገኝተዋል ተብሏል።
25 ተቋማት፣ 37 ካምፓሶች እንዲሁም 146 የትምህርት መስኮች ደግሞ የአንድ ዓመት ጊዜ ተሰጥቷቸው ቢያንስ ዝቅተኛ የሚባለውን መስፈርት እንዲያሟሉ እንደተነገራቸው ተጠቁሟል።
በተጨማሪም 62 ተቋማት፣ 66 ካምፓሶችና 256 የትምህርት መስኮች በስድስት ወር ውስጥ ዝቅተኛውን መስፈርት እንዲያስመዘግቡ የ6 ወር የጊዜ ገደብ እንደተሰጣቸውም ሰምተናል።

እኛ ይህንን የሰማነው፤ የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን እንዲሁም ትምህርት ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዳግም መዝገባና የመስክ ምልከታ ውጤት ይፋ ባደረጉበት መድረክ ላይ ነው።
በመድረኩ የተገኙ የከፍተኛ የግል የትምህርት ተቋማት ተወካዬች ዳግም ምዝገባው እንደሚደግፉት ተናግረው በተለይ አንዳንድ የተቀመጡ መስፈርቶች ካለው ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የሚከብዱ እንደሆኑ አብራርተዋል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በበኩሉ ይህ ከማድረጌ በፊት ለተቋማቱ በቂ መረጃ እና የጊዜ ገደብ ሰጥቻቸው ነበረ፤ መስፈርቶቹም በጣም ዝቅተኛ የሚባሉ እንደሆኑ ምላሽ ሰጥቷል።

በመድረኩ የተገኙት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ(ፕ/ር) የጥራት ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ ባለመሆኑ ከዚህ በኋላ የትምርት ዘርፍ እንደከዚህ ቀደሙ አይቀጥልም ብለዋል።
ለዚሁ ለጥራት ሲባል እንጂ ''እኛ የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የመዝጋት ፍላጎት ኖሮን አይደለም'' ሲሉም አስረድተዋል።
ይልቁንም የተለያዩ የትምህርት ተቋማት በጋራ በመዋሀድ ጠንካራ የትምህርት ተቋማት እንዲያቋቁሙም መክረዋል።
አዲሱ መመሪያ ሲዘጋጅ ጀምሮ የግል የትምህርት ተቋማት ሀሳብ እንዲሰጡ አድርገናል የጊዜ ገደብም ሰጥተናል ከመጀመሪያው መመሪያ አንፅር ሲታይ ይህ በጣም ዝቅ ያለ እና የመጨረሻው መስፈርት ነው ያሉት ደግሞ የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አህመድ አብተው(ዶ/ር) ናቸው።
ጨርሶ ከመስፈርቶቹ የራቁት የትምህርት ተቋማት ወደሚያዋጣቸው የንግድ ዘርፎች እንዲለውጡ ሀሳባቸውንም ሰጥተዋል።

አሁን ላይ በራሱ ፈቃድ የሚወጣ ከሆነ እንጂ የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የሚዘጋው የትምህርት ተቋም የለም ሲሉ በባለስልጣኑ የከፍተኛ ትምህርት ፈቃድ አሰጣጥ መሪ ስራ አስፈፃሚ ሕይወት አሰፋ ነግረውናል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ወደ መዝጋት ርምጃ የሚገባው አሁን እንደየደረጃቸው በ6 ወር እና በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲያሟሉ የተቀመጡ መስፈርቶች ካሳሟሉ እንደሆነው ጠቅሰዋል፡፡
ዝቅተኛ መስፈርቱን ያሟሉት ተቋማት የትኞቹ ናቸው ያልናቸው ሀላፊዋ፣ በስም ለመዘርዘር አሰራሩ እንደማይፈቅድላቸው ነግረውናል፡፡
አሁን በአዲስ አበባ ብቻ በ75 ተቋማት የተደረገው የመስክ ምልከታ በቀጣይ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙት ላይ እንደሚደረግ ተነግሯል።
ማንያዘዋል ጌታሁን
Comments