ነሀሴ 20 2017 - ''ህገ ወጥ ግንባታን ለመከላከል የተሞከሩ የመፍትሔ እርምጃዎችም ብዙም ውጤታማ አልሆኑም'' ጥናት
- sheger1021fm
- 4 hours ago
- 1 min read
በከተሞች አቅራቢያ ባሉ የማስፋፊያ ቦታዎች የሚካሄዱ ህገ ወጥ ግንባታዎች አልቀነሱም፡፡
ህገ ወጥ ግንባታን ለመከላከል የተሞከሩ የመፍትሔ እርምጃዎችም ብዙም ውጤታማ አልሆኑም፡፡
ይኽን ይፋ ያደረገው የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጥናት ውጤት ነው።
ህገ ወጥ ግንባታን ለመከላከል በአንድ ወቅት የማፍረስ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ህጋዊ እንዲሆኑ የማድረግ የመፍትሔ እርምጃዎች እንደተሞከሩ የጥናት ውጤቱን ያቀረቡት የኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ውባለም ስራው ተናግረዋል፡፡
ግን ሁለቱም መፍትሄዎች በከተሞች የሚታየውን ህገ ወጥ ግንባታ ብዙም አልቀነሰውም ብለዋል፡፡
የኢኮኖሚ ችግር፣ በህጋዊ መንገድ ቤት ለመስራት ቦታ የማግኘት ችግር ፣ እንዲሁም በመንግስት አስተዳደር ውስጥ የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለቶች ወደ ህገ ወጥ ግንባታ ሰዎችን ከሚገፉ ምክንያቶች መካከል ተብለው ተጠቅሰዋል።
በህገወጥ ግንባታ ተሳትፈው ከተገኙና ጥናቱ ከሸፈናቸው ሰዎች ውስጥ 42 በመቶዎቹ ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 40 ዓመት የሆናቸው ናቸው ተብሏል።
86 በመቶዎቹ ደግሞ ያገቡ መሆናቸው ተጠቅሷል።
ቁጥሩ ሰዎች በህገ ወጥ ግንባታ እንዲሰማሩ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ቤተሰብ መመስረት እንደሆነ ያሳያል ነው የተባለው።
በጥናቱ ከተካተቱ ሠዎች፣ ማንበብና መፃፍ የማይችሉት 13 በመቶዎቹ ብቻ ሲሆኑ 87 በመቶዎቹ እስከ መጀመሪያ ዲግሪ የሚደርስ የትምህርት ደረጃ ያላቸው መሆናቸው ተመልክቷል።
ይህም ሰዎች ስለ ህገ ወጥ ግንባታ እያወቁ ጭምር በተግባሩ እንደሚሰማሩ የሚያሳይ መሆኑ ተነግሯል ።
ንጋቱ ረጋሳ
Comments