top of page

ነሀሴ 16 2017 - የመጀመሪያው የቻይና አፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

  • sheger1021fm
  • 23 hours ago
  • 1 min read

ጉባኤው ቻይና እና አፍሪካ የሚጋሯቸው ጉዳዮች ላይ ተመስርተው የሰብዓዊ መብቶችን ለማረጋገጥ የሚመክሩበት መሆኑ ተነግሯል።


"የቻይና አፍሪካ የጋራ ማህበረሰብ መገንባትና የመልማት መብትን በጋራ ማስከበር" የሚል መሪ ቃልም ተሰጥቶታል።


ቻይና እና አፍሪካ ቅኝ ግዛትን ለመከላከል ያደረጉት ተጋድሎ፣ መከባበርና ለፍትህ ያላቸው ቀናኢነት አንድ እንደሚያደርጋቸው በጉባኤው ላይ ሲነገር ሰምተናል።


እድገት #የሰብዓዊ_መብትን ለማረጋገጥ ዋነኛው ምሶሶ ነው ለዚህም የአለም ደቡብ ሀገሮች፣ ቻይናና የአፍሪካ ሀገሮች ተመሳሳይ የልማት ሥራዎችን እና ፍላጎት ይጋራሉ ተብሏል።


ቅኝ ገዥዎች ያደረሱትን ታሪካዊ በደሎችን፣ የሀብት ዝርፊያን ሚዛኑን ያልጠበቀ ንግድ እንዲሁም የረጅም ጊዜ ሳይሳካ የቆየ የመልማት ፍላጎት የሰብአዊ መብቶች መከበር ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል በሚል በጉባኤው ላይ ተነግሯል።

ree

የመልማት መብት መሰረታዊ እና ቀዳሚ ሰብአዊ መብት ነው ያሉት ጉባኤተኞቹ ድህነትን፣ ረሃብን፣ ግጭትን እና አድሏዊ አካሄድን የመሳሰሉ እንቅፋቶችን ለማስወገድ ጥረት መደረግ አለበት ብለዋል።


ለዚህም ለቻይና እና አፍሪካ በትብብር ይሰራሉ ተብሏል።


የመልማት መብት ለማረጋገጥ ቻይናና አፍሪካ ህዝብን ያማከለ አካሄድ እንደሚከተሉ በዛሬው የመጀመሪያ በሆነው የሰብዓዊ መብት ጉባኤ ላይ ተነግሯል።


ከ2.8 ቢሊየን በላይ የሆነው የቻይና እና የአፍሪካ ህዝብ በፍትሃዊነት የመልማት መብት ማስጠበቅ ጉባኤው የመከመረበት ሌላኛው ጉዳይ ነው።


#ቻይና_እና_የአፍሪካ_ሀገራት የሰብዓዊ መብቶችን ለማክበር የየራሳቸውን ነባራዊ ሁኔታ፣ ታሪካዊ እና ባህላዊ መንገድ መምረጥ አለባቸው ሲባል ሰምተናል።


ሰብአዊ መብቶችን እንደ ምክንያት በማድረግ በሌሎች ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ለመግባት ወይም የህዝቦቻቸውን የመልማት መብት ለመንፈግ የሚደረግ ጥረትንም መቃወም እንደሚገባ በጉባኤው ላይ ተነግሯል።


በሸራተን አዲስ እየተካሄደ ባለው የቻይና አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ጉባኤ ላይ ከ200 በላይ ተሳታፊዎች ከቻይና እና ከ45 የአፍሪካ ሀገራት ተገኝተዋል ተብሏል።


ጉባኤውን የቻይና የሰብአዊ መብቶች ጥናት ማህበር፣ ዜጂያንግ ኖርማል ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በጋራ እንዳዘጋጁት ተነግሯል።


ንጋቱ ሙሉ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page