ነሀሴ 15 2017 - ኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርቷን በየስንት ዓመት መከለስ እንዳለባት ያስቀመጠችው ገደብ የለም
- sheger1021fm
- Aug 21
- 1 min read
ኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርቷን በየስንት ዓመት መከለስ እንዳለባት ያስቀመጠችው ገደብ የለም፡፡
ሥርዓተ ትምህርትን መከለስ ሲያስፈልግ ጥናት ተደርጎ መካሄድ አለበት ፡፡
አብዛኛው ሀገራት ሥርዓተ ትምህርታቸውን በየ5 ዓመቱ የሚያሻሽሉ ሲሆን ኢትዮጵያም በቅርቡ ለዓመታት የተጠቀመችበትን ሥርዓተ ትምህርት አሻሽላ ወደ ስራ አስገብታለች፡፡
በጄኔቫ ግሎባል የትምህርት ስራ አማካሪ አቶ ሳሙኤል አስናቀ መንግስት በትምህርት ዘርፍ ማሳካት የሚፈልገውን ግብ ፣ ትውልዱ ነገ ምን ዓይነት መሰረት ይዞ ማደግ አለበት የሚለውን እቅዱን ከሚያሳይበት መንገድ አንዱ የሚዘረጋው ስርዓተ ትምህርት ነው ይላሉ፡፡
አመታትን እየጠበቀ በሚከለሰው የትምህርት ካሪኩለም ውስጥ የሚቀየሩና የማይቀየሩ ጉዳዮች ዙሪያ እንደ አለም ወጥ የሆነ ስምምነት ግን የለም ብለዋል፡፡

አዲስ ወደ ስራ የገባው የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት ዋነኛ ትኩረቱ ችግር ፈቺና አምራች ዜጋን መፍጠር ነው የሚሉት አቶ ሳሙኤል አስናቀ ይህን ወደ መሬት ለማውረድ ለትምህርት ዘርፉ አጋዥ ተደርገው ወደ ስራ የሚገቡ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና አሰራሮች በተገቢው መንገድ ሊቃኙ ይገባል ሲሉም ይመክራሉ፡፡
ኢትዮጵያ የቀየረችው አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት አንድ ተማሪ የተማረውን ትምህርት ማወቅ ብቻ በቂ ነው ብሎ አያስቀምጥም፡፡
ከተማረ በኋላ ያገኘውን እውቀት ወደ ተግባር መቀየር እንዳለበት ያስቀምጣል ብለዋል ባለሙያው፡፡
ክህሎት ያለውና ብቃትን የተላበሰ ተማሪ መፍጠር ከተቻለ ኢትዮጵያ ዓለም ላይ ተወዳዳሪ የሰው ኃይልን ማግኘት ትችላለች ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ለመምህራኖች እድል መስጠትና በትምህርት ዘርፍ ላይ በሚተገበሩ ቴኮኖሎጂዎች ዙሪያ መምህሩ እንዲሰለጥን ማድረግ ይገባል የሚሉት አቶ ሳሙኤል አስናቀ የትምህርት ዘርፍ የሚጠይቀው ኢንቨስትመንት ትልቅ ነው፤ መንግስትና ህብረተሰቡ ይህን መገንዘብ አለባቸው በማለት ይናገራሉ፡፡
ሥርዓተ ትምህርቱን መሬት ላይ የሚያወርዱት መምህራን ናቸው እነሱ ላይ የሚሰራው ስራም በጥንቃቄ ታስቦና ታቅዶ ሊሆን ይገባል በማለት መክረዋል፡፡
በረከት አካሉ












Comments