top of page

ነሀሴ 13 2017 - የደመወዝ ማሻሻያ ሊደረግ ነው መባሉን ተከትሎ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች እርምጃ ይወሰዳል ተባለ

  • sheger1021fm
  • Aug 19
  • 2 min read

የደመወዝ ማሻሻያ ሊደረግ ነው መባሉን ተከትሎ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ከንግዱ ከማስወጣት በህግ እስከመጠየቅ  የደረሰ እርምጃ ይወሰዳል ተባለ፡፡


ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በኩል እንደተሰማው መንግስት ከመጪው መስከረም ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሰራተኞቹ የደመወዝ ማሻሻያ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡


በዚህም መሰረት ዝቅተኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ ከ4,760ብር ወደ 6,ዐዐዐ ብር ፣ ከፍተኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ ከብር ከ21,492 ወደ ብር ወደ 39,000 ብር እንዲሆን ተወስኗል፡፡


የዲግሪ ተመራቂዎችም መነሻ ደመወዝ ከ6,940ብር ወደ 11,500 ብር እንዲያድግ ይደረጋል ብሏል። 


የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በበኩሉ ይህ መሰማቱን ተከትሎ ህገወጦች ላይ የራሱን እርምጃ እንደሚወስድ ተናግሯል፡፡

ree

ያለ ምንም  ኢኮኖሚያዊ ምክንያት በምርቶች ላይ የዋጋ ጫማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን አልታገሳቸውም ብሏል፡፡


በሚደረገው ቁጥጥር በተለይ እጅ ከፍንጅ የሚያዙ ግለሰብና ድርጅቶች ፍቃድ ሰርዞ ከንግድ ስርዓቱ እስከ ማስወጣት የደረሰ እርምጃ ይወሰዳል፤ ድርጊቱ አጠቃላይ የንግድ ስርዓቱን የሚያዛቡ ሆነው ከተገኙ የሚወሰድባቸው እርምጃ በህግ እስከመጠየቅ እንደሚደርስ፤ የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ ነግረውናል፡፡


የሚደረገው የደመወዝ ማሻሻያ የዋጋ ንረቱ ላይ ይህ ነው የሚባል ለውጥ የሚያመጣ አይደለም፤

ምንም ዋጋ የሚያስጨምር ምክንያት አይኖርም የሚለው ሚኒስቴሩ የሰራተኛው ህይወት ላይም ለውጥ የሚያመጣ ሳይሆን፤የኢኮኖሚውን ጫና ለመቋቋም እንዲችል ታስቦ የተደረገ ድጎማ መሆኑን ጠቁሟል፡፡


ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ይህንን መሰል የደመወዝ ማሻሻያ መደረጉን ተከትሎ የሚከሰትን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር በሚኒስቴሩ የሚወሰዱ እርምጃዎች ከሳምንታት አያልፉም በሚል ይተቻል፤አሁን የሚወሰደው እንምጃ ከከዚህ በፊቱ በምን ይለያል? ያልናቸው በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ ወንድሙ ፍላቴ እንከታተላለን፤ እናስገነዝባለን ማስረጃ ያገኘንባቸው ላይ የምንወስደው እርምጃ የአንድ ሰሞን አይሆንም የሚቀጥል ነው፤እናነተም ህገ ወጦች ሲገጥሟችሁ ጥቆማ በመስጠት ተባበሩን ሲሉም ለማህበረሰቡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡


በገበያው ላይ ሊኖር የሚችለውን ህገ ወጥነት ስርዓት ለማስያዝ የሚደረግ የተለየ ዝግጅትም ይሁን ስምሪት አይሆርም፤በመደበኛው አሰራር ገበያውን እንቆጣጠረዋለን ብሏል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፡፡


በተጠናቀቀው የ2017 የበጀት ዓመት በንግድ ህጉ መሰረት ከ110,000 በላይ በሆኑ የንግድ ተቋማት  ከእስር እስከ ገንዘብ ቅጣት እንሰዲሁም የንግድ ፍቃድ የማገድና መከልከል፣ የማሸግ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ከሚኒስቴሩ ሰምተናል፡፡


ምንታምር ፀጋው

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page