ነሀሴ 13 2017 - በማሻሻያው ከ80 በመቶ በላይ ጭማሪ የተደረገው ለከፍተኛ ተከፋዮች ነው ተባለ፡፡
- sheger1021fm
- Aug 19
- 1 min read
የደመወዝ ጭማሪው ለከፍተኛ ተከፋዮች ያደላ ነው፣ በማሻሻያው ከ80 በመቶ በላይ ጭማሪ የተደረገው ለከፍተኛ ተከፋዮች ነው ተባለ፡፡
በመንግስት የተደረገው የሰራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ የተለያዩ አስተያየቶችን እያስተናገደ ነው፡፡
በጉዳዮ ዙሪያ ሙያዊ ማብራሪያቸውን የሰጡን የፋይናንስ ባለሙያው አቶ ፋሲል ጣሰው ማሻሻያው መደረጉን በበጎ እንደሚመለከቱት ጠቅሰው መሆን ነበረበት ያሉትንም ነግረውናል፡፡
ዝቅተኛ ተከፋዮችን ለመደጎም ታስቦ ከሆነ በማሻሻያው እስከ 80 በመቶ የደረሰው ጭማሪ መደረግ የነበረነበት ለዝቅተኛ ተከፋዮች ነው ብለውናል፡፡
የሆነው በተቃራኒው ነው ያሉን ባለሙያው በመንግስት ይፋ የተደረገውን መሰረት አድርገው አሰላሁት ባሉት መሰረት ለዝቅተኛው ተከፋይ 26 በመቶ ሲጨመር ለከተፍተኛው ተከፋይ ደግሞ 85 በመቶ የተጨመረው ይህ መሆኑ ተገቢ አይደለም የሚል ሃሳብ አላቸው፡፡

የኑሮ ጫናው ከአቅሙ በላይ ሆኖ አላፈናፍን ላለው፤ በቀን ሶስት ጊዜ መብላት ፈተና ለሆነበት የመንግስት ሰራተኛ ወደ ከፋ እጦት ውስጥ እንዳይገባ ለማድረግ መንግስት ያደረገው ጭማሪ የሚደገፍ ሆኖ፤ ነገር ግን ከግብር ነፃ የሚደረገው የገንዘብ መጠን ከዝቅተኛው ደሞዝ ጀምሮ ወደታች ያለው የገንዘብ መጠን ሊሆን እንደሚገባ መታሰብ እንዳለበት ያነሳሉ፡፡
ለአብነትም በዚህ ማሻሻያ ዝቅተኛው ደመወዝ 6 ሺህ ብር ከሆነ ከግብር ነፃ መሆን የነበረበትም 6ሺህ ብር ነው፤ዝቅተኛውን ደመወዝ ከግብር ካላስወጣነው ዝቅተኛ ተከፋዩን ከኢኮኖሚ ጫና ማላቀቅ አንችልም ይህ መታሰብ አለበትም ብለዋል፡፡
ከመጪው መስከረም ጀምሮ ተግባራዊ ለሚደረገው የደመወዝ ማሻሻያ 160 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው ስለሚገባ የዋጋ ግሽበቱን ሊያባብሰው ይችላል የሚሉ ባለሙያዎችን ሃሳብ እንደማቀበሉት የሚናገሩት የፋናንስ ባለሙያው አቶ ፋሲል፤ ገንዘቡ የሚከፈለው ምርታማ ለሆኑ ሰራተኞች በመሆኑ የበለጠ ምርታማነትን ይጨምራል እንጂ በራሱ የዋጋ ግሽበትን አያመጣም፤ ይህ ሲባል ግን የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈጥር ካለ የተፈራው ነገር መከሰቱ አይቀርም ለዚህም ቁጥጥር ያስፈልጋል ባይ ናቸው ባለሙያው፡፡
የደመወዝ ማስተካከያው የማይመለከታቸው በግሉ ዘርፍ ያሉ ተዋንያን ለምርታማነታቸው ማደግ ፤ በስራ ገበያው ላይ የሚገጥማቸውን ከፍተኛ ውድድር ለመቋቋም ሲሉ አቅማቸውን ያገናዘበ የደመወዝ ማስተካከያ ስለማድረግ ማሰብ አለባቸው ሲሉ መክረዋል፡፡
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s











Comments