ነሀሴ 12 2017 - ከኢትዮጵያ ህዝብ 46 በመቶ ያህሉ አሁንም ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ተራርቆ የሚገኝ ነው ተባለ።
- sheger1021fm
- Aug 18
- 1 min read
በኢትዮጵያ እስካሁን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማቅረብ የተቻለው ለ54 በመቶ ህዝብ መሆኑ ተነግሯል።
ከመደበኛው የሃይል መስመር ለሁሉም ዜጋ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ማዳረስ በተለያየ ችግር ምክንያት የማይቻል እንደሆነ ተነግሯል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች ሲናገሩ እንደሰማነው መንግስት ከአምስት ዓመት በኋላ በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር 2030 ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከቤቱ የኤሌክትሪክ ብርሃን እንዲኖረው የማድረግ ግብን አስቀምጧል።
ይህን ግብ ግን ደንበኛውን ከመደበኛው የሃይል መስመር በማገናኘት ብቻ ማሳካት የሚቻል ስላልሆነ 65 በመቶውን ከመደበኛው የሃይል መስመር፣ ቀሪውን 35 በመቶ ደግሞ መደበኛ ካልሆነ አነስተኛ የሃይል ማግኛ አማራጭ እንዲሸፈን ይደረጋል ነው የተባለው።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታው ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መስመርን በመደበኛ የሃይል አማራጭ ሙሉ ለሙሉ ለመሸፈን እንዳይቻል የሚያደርገው ምክንያት ብዙ ነው ብለዋል።
የአቅምና የገንዘብ እጥረት ችግር አንደኛው ፈተና ነው ያሉት ሀላፊው ይህ በሚበዙት የአፍሪካ ሀገራት ያለ ችግር መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እንደውም ከብዙዎቹ በተሻለ ደረጃ ላይ ነች ብለዋል።
ሌላኛው በኢትዮጵያ ያለው የተበታተነ ዓይነት ያሰፋፈር ሁኔታ ስራውን ከባድ አድርጎታል ያሉት ሀላፊው የተራራቀና የተበታተነ አሰፋፈር ባለበት ሀገር መሰረተ ልማትን ማዳረስ በጣም ከባድ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ሌላኛው የኢትዮጵያ የመሬት አቀማመጥ ተራራማ መሆን በችግርነት የሚነሳ ምክንያት ነው ብለዋል።
እነዚህ ሶስት ምክንያቶች የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ከመደበኛው መስመር ለሁሉም ማዳረስን ከባድ ያደርጉታል ብለዋል።
በእነዚህ ችግሮች ምክንያት 35 በመቶ ከመደበኛው የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ብዙ ርቆ የሚገኘው ህዝብ ኤሌክትሪክ የሚያገኘው አነስተኛ ግድቦችን በመገንባት እና እንደ የፀሀይ ሃይል ካለው ታዳሽ የሃይል አማራጭ ይሆናል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትም እስካሁን ከፀሀይ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ከሰራቸው ስራዎች 8 ሜጋ ዋት ሀይል ማግኘቱን ተናግሮ ከ100 በላይ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ደግሞ በግንባታ ላይ መሆናቸውን ነግሮናል።
ቴዎድሮስ ወርቁ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s











Comments