ነሀሴ 1 2017 -የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከዛሬ ጀምሮ እስከ መስከረም 30 በከፊል ዝግ እንደሚሆኑ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ተናገረ
- Aug 7, 2025
- 2 min read
የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከዛሬ ነሐሴ 1 ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ድረስ በከፊል ዝግ እንደሚሆኑ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባወጣው መግለጫ ተናገረ፡፡
በፌዴራል ፍርድ ቤቶች በ2017 በጀት ዓመት ለ190,347 መዝገቦች እልባት መስጠት መቻሉን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተናግሯል፡፡
በበጀት ዓመቱ ለ187,055 መዛግብት እልባት ለመስጠት በዕቅድ ተይዞ ነበር ሲልም ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡
ፍርድ ቤቶቹ በከፊል ዝግ ሆነው በሚቆዩበት የሁለት ወራት ጊዜ በባህሪያቸው አስቸኳይ የሆኑና ጊዜ የማይሰጡ በዜጎች መብትና በሀገር ልማት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩትን አቤቱታዎች እንዲሁም ለውሳኔ የደረሱ መዛግብትን መርምሮ ውሣኔ የመስጠት አገልግሎቶች ይቀጥላሉ ተብሏል፡፡
በወንጀል ጉዳዩች የሚታዩ በተለይም ህጻናት ለያዙ ሴቶችና በህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የሚመለከቱ ጉዳዮች፣ ወጣት ጥፋተኞችን የሚመለከቱ የይግባኝ ጉዳዮች፣ ለወንጀል ምርመራ በቀረበ የጊዜ ቀጠሮና ዋስትናን በሚመለከት በተሰጠ ትዕዛዝ ወይም በውሣኔ ላይ የቀረበ ወይም የሚቀርቡ የይግባኝ ክርክሮች እና አቤቱታዎች እንዲሁም ሌሎች አስቸኳይነታቸው በችሎቱ የሚለዩ መሰል ጉዳዮችን ሊያጠቃልል ይችላል ተብሏል።
በፍትሐብሔር ጉዳዮች የቀለብና ተያያዥነት ያላቸው የቤተሰብ ጉዳዮች ላይ የሚቀርብ አቤቱታና ክርክር፣ ሊያጠቃልል ይችላል ተብሏል፡፡
የሰበር አጣሪ ችሎቶች በመደበኛ ጊዜ የሚሰራውን አጣርቶ ውሳኔ የመስጠት ስራን ከነሐሴ 1ቀን 2017 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2017 ድረስ በመደበኛ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት ይቀጥላሉ ተብሏል፡፡
በተረኛ ችሎት የሚሸፈነው ጊዜ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ከጳጉሜ 1 ቀን ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ቀን 2018 ድረስ ሲሆን በፌዴራል ከፍተኛ እና መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከነሐሴ 01 ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ይሆናልም ተብሏል፡፡
ከጥቅምት 1 ቀን 2018 ጀምሮ ዳኞች በመደበኛነት በተመደቡበት ችሎት ተገኝተው በክረምት የተሰሩ ውሣኔዎችን ለተከራካሪዎች ለመግለፅ የሚዘጋጁበት ጊዜ በመሆኑ ከዚህ ቀን ጀምሮ የሚቀርቡ አቤቱታዎችና ሌሎች ጥያቄዎች በመደበኛው ችሎቶች የሚስተናገዱ ተነግሯል፡፡
በክረምት የእረፍት ጊዜ ውሣኔ ያገኙ መዛግብት ከጥቅምት 3 ቀን 2018 እስከ ጥቅምት 7 ቀን 2018 ድረስ ለተከራካሪ ወገኖች በችሎት የሚገለጽ ሲሆን በእነዚህ ቀናት ባለጉዳዮች እንዲቀርቡና ውሣኔያቸውን እንዲሰሙ በስልክ ወይም አጭር የጽሁፍ መልእክት እስከ መስከረም 8 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ባሉት ቀናት እንዲያውቁ ይደረጋል ሲል ጠቅላይ ፍርድቤት ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል፡፡
በረከት አካሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyu.com/ycxjmm3s





Comments