ነሀሴ 1 2017 - በነሐሴና በመስከረም ወር የሚኖረው የዝናብ መጠን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የአፈር መሽርሽርንና የመሬት መንሸራተትን ሊያስከትል እንደሚችል ተነገረ
- sheger1021fm
- Aug 7
- 1 min read
በነሐሴና በመስከረም ወር የሚኖረው የዝናብ መጠን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የአፈር መሽርሽርንና የመሬት መንሸራተትን ሊያስከትል እንደሚችል ተነገረ።
ይህን ያለው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ነው።
ነሀሴ እና መስከረም ወር ላይ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ እና ከባድ ዝናብ እንደሚኖራቸውም በትንበያው መረጃ ተናግሯል፡፡
የዝናብ መጠኑን ተክትሎም የአፈር ውስጥ እርጥበት መብዛትና፣ በማሳዎች ላይ የውሃ መተኛትና በረባዳማ አካባቢዎች የሰብሎች በውሀ መዋጥ ፣ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ የከተማም ሆነ የገጠር አካባቢዎች የቅጽበታዊ ጎርፍ መከሰት፣ በተደጋጋሚ የወንዝ ሙላት፣ እንዲሁም የወባ ተጋላጭ በሆኑት አካባቢዎች ላይ ለወባ ትንኝ መፈጠርና ማደግ አመቺ የአየር ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም ተነግሯል።
የክረምት ወቅት ዝናብ አወጣጥም በደቡብ ምዕራብ ፤ በምዕራብ ፤ በሰሜን ምዕራብ እና በመካከለኛው የኢትዮጵያ አከባቢዎች የመዝግየት አዝማሚያ እንደሚኖረውም ተመላክቷል ፡፡
ኢንስቲትዩቱ የነሀሴን እና የመስከረምን የዝናብ መጠን ተከትሎ የሚኖረው በአዎንታዊ የሚኖረው ተጽዕኖን በተመለከተ ለመኸር ሰብሎች በቂ የአፈር ውስጥ እርጥበት እንዲኖር ማስቻል፣ የተለያዩ የሰብል አማራጮችን ለመዝራት የሚያስችል በቂ የሆነ እርጥበት ይኖራል፡፡
በመደበኛ ሁኔታ እርጥበት አጠር የሆኑ አካባቢዎች የዝናብ ውሃን ለማሰባሰብ እና ለማከማቸት ያስችላል ብሏል።
የግድቦች የውሃ መጠን እንዲጨመር እና የገጸ ምድር እና የከርሰ ምድር የውሃ ሀብትን እንዲሁም የተለያዩ የተፈጥሮም ሆነ የሰው ሰራሽ ምንጮችን እንዲጎለብቱ ያደርጋልም ተብሏል።
ባለፉት ሁለት ወራት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ የነበራቸው ሲሆን በአጠቃላይ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ከደመበኛ በላይ የዝናብ መጠንና ሥርጭት እንደነበራቸውም ኢንስቲትዮቱ ተናግሯል።
በቀጣይ ከሚኖረው ተደጋጋሚነት ያለው ከባድ ዝናብ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሥራዎች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ እንዲያስችል አስፈላጊውን የጥንቃቄ ስራ ከወዲሁ መከናወን እንዳለበትም ተናግሯል፡፡
ፍቅሩ አምባቸው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyu.com/ycxjmm3s
Comments