#ታሪክን_የኋሊት
- 6 hours ago
- 2 min read
የኢትዮጵያ የመጨረሻው ንጉሠ ነገሥት፣ አጼ ኃይለ ስላሴ የተወለዱት፣ በ1884 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡

ከመንገሳቸው በፊት “ተፈሪ” በሚለው ስማቸው የሚታወቁት አጼ ኃይለ ሥላሴ፣ የአስተዳደር ስልጣን የጀመሩው ገና በ14 አመታቸው ነበር፡፡
አባታቸው የሃረሩ ገዥ ራስ መኮንን ወልደሚካኤል የጋራሙለታ አውራጃ ገዥነትን በእንደራሴ እንዲያስተዳድሩ ከሾሟቸው በኋላ፣ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ፈቃድ የሰላሌን የሲዳማን ግዛት አስተዳድረዋል፡፡
ለአልጋ ወራሽነት በጦር አለቆች ከመመረጣቸው በፊትም የሐረር ጠቅላይ ገዥ ነበሩ፡፡
ለአልጋ ወራሽነት ለመመረጥ የበቁት፣ የጦር አዛዦቹ ልጅ ኢያሱን ተቃውመው ከመንግስት ስራ ሲያስወጣቸው፣ ባህሪያቸውንና የቀድሞ የሥራ ልምዳቸውን ገምግመው ፣ከንግስት ዘውዲቱ ህልፈት በኋላ ንጉሥ እንደሆኑ ሰየሟቸው፡፡
ራስ ተፈሪ፣ አንድ ጊዜ የሥልጣን ወንበሩን በሌሎች ርዳታ ከተቆናጠጡ በኋላ ስልጣናቸውን ለመጠበቅ፣ ብልህና ጠንካራ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
ይቃወሙኛል ያሏቸውን በሹመት እየደለሉና በቅጣትም እያስፈራሩ፣ ስልጣናቸውን አጠናክረው የንጉሥ ነገስትነቱን ዘውድ ጫኑ፡፡
መንግስት ደንግገው በስርዓት ለመምራት ችለዋል፡፡ አፄ ኃይለስላሴ ፣የኢጣሊያን ወራሪ ጦር፣ ማይጨው ላይ ተዋግተው ከተሸነፉ በኋላ ወደ እንግሊዝ ሃገር ተሰደዱ፡፡
በመንግስታቱ ማህበር አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ከአምስት አመታት በኋላ በድል አድራጊነት ወደ ስልጣን ከተመለሱ በኋላ ሃገሪቱ ዘመናዊ አስተዳደር እንዲኖራት ውጤት ያለው ጥረት አድርገዋል፡፡
ዘመናዊ የመከላከያ ሀይል አቋቁመዋል፤ ኢትዮጵያ ከውጭ አለም ጋር ያላት ግንኙነት የተጠናከረ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሲመሰረት ከመስራቾቹ ሃገር እንድትሆን አድርገዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትርነቱን ይዘው ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፉ፣ ዩኒቨርስቲው በግል ቤታቸው እንዲቋቋም በማድረግ የታወቀ ጥረት አድርገዋል፡፡
በዲፕሎማሲ ጥረት ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ እንድትቀላቀልና በእንግሊዞች ተይዞ የነበረውን የኡጋዴንና የጋምቤላን ግዛት ፣ወደ ቀድሞ ይዞታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ችለዋል፡፡
የእንግሊዞችን ተፅዕኖ በዲፕሎማሲ ተልዕኮ ብቻ ሲያቃልሉ፣ ከሶማሊያ ጋር የተደረገውን ጦርነት በሀይል ደምስሰዋል፡፡
በሌላ በኩል ከኢጣሊያ ወረራ በኋላ ባሉት የ33 አመታት የስልጣን ቆይታቸው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቶች እንዲያቆጠቁጡ ባለማድረጋቸው ተተቹ፡፡
በተለይም የጭሰኛና የባለርስትን ግንኙነት የሚያሻሽል ሥርዓት ባለመፈጠራቸው ተወቀሱ፡፡
የተማሪዎችም እንቅስቃሴ በአገዛዛቸውን ኃላቀርነት የሚያወግዝ ሆነ፡፡
በመጨረሻው የተቀሰቀሰባቸውን የየካቲት 66 የህዝብ አመፅ ፣ተገን አድርገው ለስልጣን የተሰባሰቡት የወታደሮች ኮሚቴ፣ ከስልጣን አወረዳቸው፡፡
ከአንድ አመት እስር በኋላም ገደላቸው፡፡ 43 አመታት የነገሱትና በ84 አመታቸው በደርግ የተገደሉት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከተወለዱ፣ 134 አመት ሆነ፡፡
እሸቴ አሰፋ
_edited.jpg)



Comments