top of page

ታሪክን_የኋሊት

  • 1 hour ago
  • 2 min read

ሐምሌ 7/2018


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፣ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ፣ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉት ፣በ1971 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡


ፓርትርያክ ብፁዕ ወቅዱስ አባ ቴዎፍሎስ በግፍ የተገደሉት በኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም በሚመራው ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ትዕዛዝ ነው፡፡


ደርግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፣ የንጉሱን አስተዳደር የምትደግፍና ፣ ለሶሻሊዝም ሥርዓት እንቅፋት ነች ብሎ ስላመነ ፣ ለማጥቃት የሚፈልግበትን መንገድ ሲያደራጅና የስም ማጥፋት ፕሮፓጋንዳ ሲያከናውን ቆየ፡፡


ከአንድ አመት በኋላም ፓትርያርኩንና ሊቃነ ጳጳሳትን አሰረ፡፡


ብጹዕ ወቅዱስ አባ ቴዎፍሎስ ፣ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ሆነው የተሰየሙት፣ የመጀመሪያውን ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ፣ ብጹዕ ወቅዱስ አባ ባሰልዮስን ተክተው ነው፡፡



ከዚያ በፊትም የሀረር ሊቀ ጳጳስና የፓትርያርኩ እንደራሴ ሆነው በጠቅላላው ለ20 አመታት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን በሀላፊነት አገልግለዋል፡፡


ብጹህ ወቅዱስ አባ ቴዎፍሎስ ፣ በፕትርክና ዘመናቸው ፣ ቤተ ክርስቲያኗ ራሷን ችላ ለመተዳደር የሚያበቃትን ፣ የሰበካ ጉባኤ አደረጃጀት አስጀምረዋል፡፡


የአለም ዐብያተ ቤተ ክርስቲያን ምክር ቤት አባል አድርገዋል፡፡


የቤተ ክርስቲያኗ ልማት እንዲስፋፋ የልማት ተራድኦ ኮሚሽንን አቋቁመዋል፡፡


ሃይማኖት የለሽ መሆንን መመሪያው ያደረገው ወታደራዊው መንግስት ፣ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ ቢናገርም፣ ግን የሃይማኖት ተቋሞችን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን አሰራር ዘርግቶ ነበር፡፡


ስለዚህ ፓትርያርኩንና ሌሎች ጳጳሳትን የሌሎች ሃይማኖት መሪዎችንም አሰራቸው፡፡


ከቤታቸው በወታደሮች ተወስደው የታሰሩት ብፅዕ ወቅዱስ አባ ቴዎፍሎስ ከታሰሩበት ቦታ ለማምለጥ ችለው ነበር፡፡


ወደ አሰቦት ገዳም ለመሄድ ስላሰቡ ፣ ለጉዟቸው ዝግጅት ለማድረግ ጎፋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተሸሸጉ፡፡


ግን በጎፋ ገብርኤል ግቢ መሆናቸውን ፣ የሚያውቅ ሰው ከድቶ ፣ ለደርግ ጠቆመ ተያዙ፡፡ በወታደሮች ሲያዙ፣ ብዙ ግፍ ፈፀሙባቸው፡፡


ጫማቸውን አስወልቀው በእግራቸው አስኬዷቸው፡፡ለአንድ ወር ያህል በአንዲት ጠባብ ጨለማ ክፍል አስገብተው ፣ እጃቸውንና እግራቸውን ከአልጋ ጋር በሰንሰለት አሰሯቸው፡፡


የሚይዙትን የወርቅ መስቀል ወሰዱባቸው፡፡ ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ፣ በታላቁ ቤተ መንግስት ቀዝቃዛ የምድር ቤት ፣ ቁጥር 1 እስር ቤት ለሶስት አመታት ፣ከሌሎቹ የንጉሱ ሹማምንት ጋር አስሯቸው፡፡


ሁሉንም በፀጋ እየተቀበሉ ፣ አብረዋቸው የታሰሩትን ያፅናኑና በፀሎት ይረዱ ነበር፡፡ በ1971 ዓ.ም ከሐምሌ አምስት ጀምሮ ፣ የንጉሱን ከፍተኛ ሹማማንት ለመግደል ከእስር ቤት ሲወስዳቸው፣ ቅዱስ ፓትሪያርኩ ሟቾቹን እያናዘዙ በፀሎት ሲሸኙ ሰነበቱ፡፡


ሐምሌ 7/1971 ደርግ ፣ ፓርትርያርኩንና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት የነበሩት ደጃ ካሳና ሌሎችንም ጨምሮ በምሽት ጠሯቸው፡፡


ቅዱስ ፓትርያርኩ ፣ ፀሎታቸውን አድርሰው ፣ ጥቁር ቀሚሳቸውንና ቆባቸውን ደፍተው ፣ የቀሩትን እስረኞች ባርከው ፣ ወደ አሳሪዎቻቸው ሄዱ፡፡


የደርግ ወታደሮች ፣ ቅዱስ ፓትርያርኩንና 15 የሚሆኑን ሹማምንት ፣ የራስ አሰራተ ካሳ መኖሪያ ወደነበረበት ገነተ ኢየሱስ አካባቢ ወስዷቸው፡፡


በግቢው ውስጥ በጨለማ እንዲያልፉ አስገደዱዋቸው በመሄድም ላይ እንዳሉ፣ በጨለማ የተደበቁ ገዳዮች ፣ አንገታቸውን በኤሌክትሪክ ሽቦ አንቀው ገደሏቸው፡፡


ከሌሎች ተገዳዮች ጋር ለምሽግ በተቆፈረው ጉድጓድ ጣሏቸው፡፡


የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም መንግስት ተባሮ ፣ ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝ ፣ቅዱስ ፓትርያክ አባ ቴዎፍሎስ ከሌሎች ጋር የተቀበሩበት ቦታ በጥቆማ ተገኘ፡፡


ከአፅማቸው ጋር ጥቁር ቀሚሳቸውና የምንኩስና ቆባቸው ተገኘ፡፡ በተገደሉ 13 አመታት በኋላ አፅማቸው ፈልሶ፣ በሙሉ ክብር በአሰሩት በጎፋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የሰማዕትነት ክብር ሰጥታቸው በጎፋ ገብርኤል ሐውልት ተቀርጾላቸው፣ ሙዚየምም፣ ተሰርቶላቸዋል፡፡


ሁለተኛው የኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ፣ ብጹዕ ወቅዱስ አባ ቴዎፍሎስ ፣ በ69 አመታቸው ሰማዕትነት ከተቀበሉ ፣ 47 አመት ሆነ ፡፡


እሸቴ አሰፋ

Recent Posts

See All
ኢትዮጵያ በ2018 በጀት አመት በ9 ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢን አግኝታለች፡፡

ሐምሌ 7/2018 ኢትዮጵያ በ2018 በጀት አመት በ9 ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢን አግኝታለች፡፡ ከውጪ አስፈላጊ ለምትላቸው እቃዎች ግዢ 16 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ አውጥታለች፡፡ በዘጠኝ ወራቱ ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ከላከችው እቃ ያገኘችው ገቢና ወደ ሀገር ውስጥ ላስገባችው እቃ ያወጣች

 
 
 
ሐምሌ 7/2018 - ዓለም አቀፍ ወሬዎች

#ኢራን የኢራን አብዮታዊ ዘብ የቀድሞ አዛዥ ሆሴን ካናኒ የአሜሪካውን ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕን ዋይት ሐውስ ድረስ ዘልቀን እንገድለዋን ሲሉ ዛቱ፡፡ ካናኒ ኢራን ደግሞ ለዚህ አቅሙም ችሎታውም አላት ማለታቸውን ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡ በቅርቡ ለሟቹ የኢራን የቀድሞ ጠቅላይ መሪ ስንብት እና የቀብር ሥነ ሥርዓት

 
 
 
Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page