top of page

ታሪክን የኋሊት - ግንቦት 5፣2017 - ከኢጣሊያ ወረራ በኋላ ፣ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መቋቋሙ ይፋ የሆነው በ1933 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡

  • sheger1021fm
  • 23 hours ago
  • 2 min read

አጼ ኃይለሥላሴ በድል አድራጊነት፣ አዲስ አበባ ከገቡ ስምንት ቀናት በኋላ፣ የሰየሙትን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለማቋቋም፣ ከፍተኛ ፈተና ተደንቅሮባቸው ነበር፡፡


አዲስ አበባን ቀድመው የተቆጣጠሩት እንግሊዞች ፣ ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት ሆናለችና የእንግሊዝ ይዞታ መሆን አለባት የሚል እምነት ነበራቸው፡፡


በተለይም የጦር የፖለቲካ ሀላፊዎች የኢትዮጵያ ነፃ መሆንና ንጉሥ ነገስቱ የመቆጣጠር ስልጣን እንዳይኖራቸው ፣ በተግባር የተደገፈ መሰናክል ይፈጥሩ ነበር፡፡


አዲስ አበባን ጨምሮ ፣ ቀድመው በያዟቸው ቦታዎች ፣ኢጣሊያኖች ጥለውት የሄዱትን መሳሪያና ብር እየዘረፉ ነበር፡፡


ከአርበኞችም ጋር እየተጋጩ እስከ መታኮስ ደርሰዋል፡፡


ኢትዮጵያ በበኩሏ፣ ከእንግሊዝ መንግስት ጋር በደረሰችበት ስምምነት መሰረት፣ ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠ መሆኑን ለማሳየት ተንቀሳቀሰች፡፡


በቅድሚያ የእንግሊዞችን ስሜት ለማረጋገጥ፣ አዲስ አበባን ለተቆጣጠረው የእንግሊዝ ጦር አዛዥ ለጀኔራል ካኒግሃም የሜዳሊያ ሽልማት ለመስጠት ቢፈልጉ “አይመቸኝም” ብሎ ለመቀበል አለመፈለጉን አሳየ፡፡


እውቅና አለመስጠቱን የሚያመለክት ነበር፡፡


አፄ ኃ/ሥላሴ ሌላ ርምጃ ለመውሰድ ወሰኑ፡፡


ለእንግሊዝ ፖለቲካ ሀላፊዎች ሳያሳውቁ ፣ሰባት አባላት ያሉት የሚኒስሮች ካቢኔ መሰረቱ፡፡


በጊዜው የተሾሙት ሰባት ሚኒስትሮች ቢቶደድ መኮንን እንዳልካቸው የሃገር ግዛት፣ ፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደጊዮርስ ወልደዮሐንስ የፅህፈት ፣ ብላቴን ጌታ ሎሬንሶ ትዕዛዝ የውጭ ጉዳይ፣ አቶ መኮንን ደስታ የትምህርት ፣ አቶ አየለ ገብሬ የፍርድ ፣ አቶ በላቸው ያደቴ የፖስታና ቴሌ፣ ነገድረስ ገብረእግዚአብሔር ደስታ የንግድ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ፡፡


በጥድፊያ የተደረገው ሹመት ከእንግሊዞች ጋር ለመፈታተን ስለሆነ የጦር ሚኒስትርና ጠቅላይ ሚኒስትርን የመሰሉ ከፍተኛ የስራ መደቦች አልተሾሙም፡፡


በድንገት የተደረገውን ሹመት የሰማው የእንግሊዝ የፖለቲካ ሀላፊ፣ በቁጣ ግሎ፣ ቤተ መንግስት ድረስ ሄዶ ንጉሱን “ማን እንድትሾሙ ፈቀደላችሁ?” ብሎ ተቆጣቸው፡፡

አፄ ኃይለስላሴም “ሃገሬ ነፃ ናት እናንተም የጦር ረዳቶቻችን እንጂ ገዥዎች አይደላችሁም” ብለው መለሱለት፡፡


ካቢኔውን እንዲበትኑ የሰጣቸውንም ማስጠንቀቂያ ውድቅ አደረጉት፡፡



ነገር ግን ንጉሰ ነገስቱ ነፃ ሃገር ነን ቢሉም ፣በዘመናዊ የጦር ሀይል ብልጫ ያላቸውና ሁሉንም መገናኛ የተቆጣጠሩት እንግሊዞች የበላይነቱን እንደያዙ ቆዩ፡፡


እንግሊዞች፣ ፋይናንሱን የውጭ ጉዳይን የፖሊስ ሀይሉን ፣ የፍትህ ሥዓቱን ተቆጣጣሪ ሆነው፣ ሁለት አመት ቆይተዋል፡፡


የተጀመረው የሚኒስትሮች ሹመት ግን አልተቋረጠም ፡፡


በየጊዜው የተሾሙት ሚኒስትሮች ፣ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ትግል አድርገው የእንግሊዝ የበላይነት ቀርቶ ፣ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሃገር መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

ከኢጣሊያ የአምስት አመት ወረራ በኋላ፣ ኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ካቋቋመች ፣84 ዓመት ሆነ፡፡


እሸቴ አሰፋ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…






Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page