top of page

ታሪክን የኋሊት - ንግስተ ነገስታት ንግስት ዘውዲቱ

  • 2 hours ago
  • 2 min read

በኢትዮጵያ የመሪዎች ታሪክ ፣ ባለፉት 1000 ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያዋ ሴት ንግስተ ነገስታት የነበሩት ንግስት ዘውዲቱ ፣ ያረፉት በ1922 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡


ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ፣ በ10ኛ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ መሪ እንደነበረች ከሚነገርላት ዮዲት ጉዲት ወዲህ ፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሴት መሪ ነበሩ፡፡


ንግስት ዘውዲቱ ፣ የኢትዮጵያን ንግስና ያገኙት ፣ በጊዜው የነበሩት የጦር አለቆች ፣ አገረ ገዥዎች ፣ መኳንንት የቤተ መንግስቱ የጥበቃ ወታደሮች ምርጫ እንጂ እንደቀደምቶቻቸው በውርስና በውጊያ አልነበረም፡፡


ከአዲስ አበባ ቤተ መንግስት የተላኩ የጦር መኮንኖች ፣ መሳፍንቱ መኳንንቱ ሕዝብና ሰራዊት፣ በአንድነት ተስማምተው ፣ ነግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ተብለው ፣ በአባትዋ በአፄ ምኒልክ ዙፋን እንዲቀመጡ “መርጦዎታል” ተብለው የተነገሩት አዳበርጋ አካባቢ ፣ፋሌ ከሚባለው ፣ ቦታቸው ከባላቸው ራስ ጉግሳ ወሌ ጋር በግዞት ተቀምጠው ሳለ ነበር፡፡


#ንግስት_ዘውዲቱ የተወለዱት፣ በ1860 ዓ.ም ነው ይባላል፡፡ ገና በታዳጊነታቸው ፤ ለዚያን ጊዜው ንጉሠ ነገስት ዩሐንስ 4ኛ ልጅ፣ ለራስ አርኢያ ዩሐንስ ተዳሩ፡፡ የፖለቲካ ጋብቻ መሆኑ ነው፡፡


ራስ አርእያ ከሞቱ በኋላ፣ በሸዋ ደጃ ውቤን አገቡ፡፡


አባታቸው፣ ምኒልክ ንጉሠ ነገስት ሲሆኑ የእቴጌ ጣይቱን የወንድም ልጅ፣ ራስ ጐግሳ ወሌን አገቡ፡፡ አባታቸው እስከታመሙ ድረስም፣ በባላቸው የግዛት ሃገር ደብረታቦር ኖሩ፡፡


ዳግማዊ አፄ ምንኒልክ፣ ሲታመሙ፣‹‹ አባቴን አስታምማለሁ››፤ ብለው ትዳራቸውን ትተው፤ አዲስ አበባ ቆዩ፡፡

አባታቸው ከሞቱ በኋላ ፣ ልጅ ኢያሱ፣ እንደ ስልጣን ተቀናቃኝ አይተዋቸው፣ ከቤተመንግስት ብቻ ሳይሆን፣ ከአዲስ አበባም አስወጧቸው፡፡


የጦር አዛዦች “ልጅ ኢያሱ፣ ለመሪነት አይበቁም፣” ብለው ከስልጣን ሊያባርሩዋቸው ሲያቅዱ፣ ዙፋኑን መያዝ ያለበት የምኒልክ ዘር ነው አሉ፡፡ በጊዜውም በሕይወት ያሉት ልጃቸው፣ ዘውዲቱ ብቻ ነበሩና የሁሉም ምርጫ በርሳቸው ላይ አዘነበለ፡፡


የኢትዮጵያ መንግስት ንግስተ ነገስታት መሆናቸውን አዋጁ ከታወጀ ሁለት ቀናት በኋላ የሰሙት ንግሥት ዘውዲቱ የውጭ ሃገር ፊልም ቀራፂዎች በተገኙበት ከፍ ባለ ሥነ ሥርዓት ንግሥናቸው ተከበረላቸው፡፡


በስልጣን ዘመናቸው መጀመሪያ፣ ከተደረገው የሰገሌ ጦርነትና በስልጣን መጨረሻቸው ዓመት ከተደረገው የቋና ጦርነት በስተቀር፣ ዘመነ መንግስታቸው ሰላም ነበር፡፡ 13 አመታት ከስድስት ወራት ኢትዮጵያን መርተዋል፡፡


በርሳቸው የንግስና ዘመን፣ አዳዲስ የስልጣኔ ግኝቶች ተጀምረዋል፡፡


በአባታቸው ጊዜ የተጀመሩትም በጥቂቱም ቢሆን ተሳፋፍተዋል፡፡


እንደራሴና አልጋ ወራሽ ሆነው፣ የተመረጡት፣ ራስ ተፈሪ፣ ቀስ እያሉ ስልጣናቸውን እየሸራረፉ ለመጠቅለል የሚያደርጉትን ርምጃም፣ በትዕግስት እያለፉ ግጭቶች እንዳይከሰቱ አድርገዋል፡፡


ንግስት ዘውዲቱ፣ “በዘመኔ የርስ በርስ ጦርነት ሆኖ” ፣ ደም ከሚፈስና በዚህ ሰብብ የውጭ ወራሪ ኢትዮጵያን ከሚገዛት ፣የተጠየቅሁትን ስልጣን እየለቀቅሁ፤ ብኖር ይሻለኛል፤” ይሉ ነበር ይባላል፡፡


ንግስት ዘውዲቱ፣ የግል ዝናን የሚፈልጉ ስላልነበሩ፣ የመስሪያ ቤቱ ስራ ሁሉ የሚካሄደው በአፄ ምኒልክ ስም፣ ነበር፡፡ በመልካቸው የተቀረፀውን ሳንቲም ለመታሰቢያ ብቻ እንዲታተም አድርገው፣ የአባታቸው ምስል፣ ያሉባቸው ሳንቲሞች እንደቀጥሉ አድርገዋል፡፡


የደቡብ ጎንደር ገዥ የነበሩት ባለቤታቸው ራስ ጉግሳ ወሌ፣ በራስ ተፈሪ አስተዳደርና ‹‹በዘውዲቱ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠሩ ነው›› የሚል ግምት ስለነበራቸው አመፁ፡፡ ባልና ሚስቱ ፣ በተለያዩ የፍልሚያ ጐራ ተሰለፉ፡፡


ራስ ተፈሪ፣ ራስ ጐግሳን የሚወጋ ጦር ወደ ቋና ላኩ፡፡ በቋና በተደረገው ውጊያም ራስ ጉግሳ መጋቢት 22 ሞቱ፡፡


በዚያ ወቅት፣ በአዲስ አበባ ቤተመንግስት የሚገኙት፣ ንግስት ዘውዲቱ ታመው ነበር፡፡ ለመጋቢት 24 አጥቢያ፣ 1922 ፣አርብ ቀን አረፉ ፡፡


ንግስት ዘውዲቱ ሲሞቱ ፣ የቀድሞ ባላቸውን የራስ ጉግሳን በጦርነቱ ላይ መሞት አልሰሙም ነበር፤ ይባላል፡፡


ግንባታውን ከፍፃሜ አድርሰው ፣ የመመረቂያ ቀኑን የሚጠብቁለትን የአባታቸውን ሃውልትና የአባታቸው አፅም የሚርፍበትን የታዕካ ባዕታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያንን ሳይመርቁ ሞቱ፡፡


ንግስት ነገስታት ዘውዲቱ፣ በማግስቱ በታላቅ ክብር ፣በይፋ የቀብራቸው ስነ-ስርዓት ለአባታቸው አፅሞ ማረፊያ ባሰሩት ፣የታዕካ ነገስት ባዕታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ተፈፀመ፡፡


በኢትዮጵያ የነገስታት ታሪክ፣ ከዘመነ መሳፍንት ወዲህ፣ በይፋና በክብር ለመቀበርም ፣ንግስት ዘውዲቱ የመጀመሪያዋ ንግስተ ነገስታት ናቸው፡፡


ይኸ ከሆነ ዛሬ 96 ዓመት ሆነ፡፡


መጋቢት 24/2018


እሸቴ አሰፋ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


YouTube : https://shorturl.at/18TS1

WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx

X :- https://x.com/shegerfm?s=2

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page