ታሪክን የኋሊት -ራውል ካስትሮ የኪዩባን መሪነት ስልጣን ፣ ከፊደል ካስትሮ የተረከቡት ቀን
- sheger1021fm
- Jul 31
- 2 min read
ራውል ካስትሮ የኪዩባን መሪነት ስልጣኑን ከወንድማቸው፣ ከፊደል ካስትሮ የተረከቡት በ1998 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡
#ራውል_ካስትሮ ኪዩባን ለ48 ዓመታት የመሩት የፊደል ካስትሮ፣ ወንድም ሲሆኑ በትጥቅ ትግሉ ጊዜም አብረዋቸው ነበሩ፡፡
በፊደል ካስትሮ የሚመሩት፣ 160 ወጣት ኮሚዩኒስቶች ጠመንጃ አንስተው፣ የጀኔራል ባቲስታን መንግስት ለማስወገድ፣ ባደረጉት ትግል፣ ራውል አንደኛውና የወንድማቸውን ትዕዛዝ ለመፈፀም ፣ቆራጥ ተዋጊ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡
ኮሚዩኒስቶቹ ኩባውያን ከገጠር ወደ ከተማ ባደረጉት ትግል፣ ቀንቷቸው ስልጣን ያዘ፡፡
ፊደል ካስትሮ፣ የኮሚዩኒስት ፓርቲው ዋና ፀሐፊና የኪዩባ ፕሬዘዳንት ሲሆኑ ራውል የፖሊት ቢሮ፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የመከላከያ ሚኒስትር ሆኑ፡፡
አንዳንድ ፀሐፊዎች፣ ራውል ካስትሮ ከታላቅ ወንድማቸው ከፊደል ይልቅ ብርቱና ጨካኝ ፣ ተናግረው ከማሳመን ይልቅ ሀይል የሚመርጡ ያደርጓቸዋል፡፡
የኪዩባን የመከላከያ ሀይል በአዲስ መልክ ለማደራጀት ለ50 አመታት ያህል በከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውና ለ50 አመታት ያህል በጀኔራልነት ማዕረግ መምራታቸው ይታወቅላቸዋል፡፡
ወንድማቸውን ፊደልን ፣ የሃገሪቱ አባት ፣ ውድ መሪያችን፣ ታላቁ መምህራችን፣ በሚል ቅፅል በየስብሰባው የሚጠሩና ታማኛቸው ነበሩ፡፡

ፊደል ካስትሮ ፣እርጅና ሲጫጫናቸው የፓርቲውን ዋና ፀሐፊነትና ፕሬዘዳንትነቱን ያስረከቡት በታማኝነት ላገለገሏቸው ወንድማቸው ራውል ካስትሮ ነበር፡፡
ራውል ካስትሮ፣ አመራራቸው ከፊደል ተመሳሳይ ሲሆን በምጣኔ ሀብት ፖሊስ ከዕዝ ኢኮኖሚ በከፊል እንዲላቀቅና የግሉ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር አድርገዋል፡፡
ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን የሻከረ ግንኙነት ለማለሳለሱ ሞክረዋል፡፡
ከኦባማም ጋር ተነጋግረዋል፡፡
ራውል ኪዩባን በፕሬዘዳንትነት ለ10 ዓመታት በኮሚዩኒስት ፓርቲ ፀሐፊነት ለአስራ ሶስት አመታት ከመሩ በኋላ፣ 89 አመት ሲሆናቸው በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ለቀቁ፡፡
ለኮሚዩኒስት ፓርቲው ታማኝ ነው ብለው ቀደም ብለው ፕሬዘዳንትነቱን ያስረከቧቸው የ60 አመቱ ሚጌል ዲያዝ ካኔል ተኳቸው፡፡
ከስልጣን መልቀቃቸውን ለማዕከላዊ ኮሚቴ ባስታወቁበት ወቅት “ስልጣን እንድለቅ ማንም ማንም አላስገደደኝም፣ በሕይወት እስካለሁ አባት ሃገርን ፣ አብዮቱንና ሶሻሊዝምን ለመከላከል እቆማለሁ” አሉ፡፡
የራውል ስልጣን መልቀቅ የካስትሮ ልጆች የስልጣን ዘመን ማጠናቀቂያ ሆነ፡፡
ራውል ሀላፊነታቸውን ካስረከቡ በኋላ በመድረክ ፊት አልታዩም፡፡
አሁን 95 ዓመት ሆኗቸዋል፡፡
የሽምግልና እድሜያቸውን በቤታቸው ያሳለፉ ነው፡፡
ራውል ካስትሮ ከወንድማቸው ከፊደል ስልጣን ከተረከቡ ፣ 17 ዓመታት ሆነ፡፡
እሸቴ አሰፋ
ሐምሌ 24 2017
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s








