ታህሳስ 3/2018 የሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ሃይል ፍጆታ ካለፈው ሃምሌ ወር ወዲህ እያደገ መጥቷል ተባለ።
- sheger1021fm
- 15 minutes ago
- 1 min read
ኢትዮጵያ ከተለያዩ ምንጮች ከምታመርተው የኤሌክትሪክ ሃይል 90 በመቶው ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል እንደሆነ ተጠቅሷል።
በዘንድሮው በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ አራት ወራት ኢትዮጵያ ከውሃ እና ከነፋስ ከ15,300 ጊጋዋት ሰዓት በላይ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨቷ ተነግሯል።
በየወሩ በአማካይ 3,800 ጊጋዋት ሰአት የኤሌክትሪክ ሃይል አመንጭታለች እንደማለት ነው።
ከመነጨው የኤሌክትሪክ ሃይል ከ90 በመቶ ያላነሰው ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እንደዋለ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ነግረውናል።
የሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ሃይል ፍጆታ ከጊዜ ወደ እያደገ መጥቷል ያሉት ዳይሬክተሩ ከሃምሌ ህዳር የነበረው መረጃ ይህንኑ እንደሚያሳይ ጠቁመዋል።
በሀገር ውስጥ ያሉ የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚዎች በቤት ውስጥ ካሉ ደንበኞች እስከ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ያሉትን የሚያካትት እንደሆነ አቶ ሞገስ ተናግረዋል።
በአራት ወራቱ ለሀገር ተጠቃሚዎች በሽያጭ ከቀረበ የኤሌክትሪክ ሃይል ከ14 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱንም አቶ ሞገስ ነግረውናል።
ወደ ኬንያ ፤ ታንዛንያ እና ጁቡቲ ከተላከ የኤሌክትሪክ ሃይል ደግሞ ከ 46 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷን ብለዋል።
ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል ከሚገዙ ሀገራት አንዷ ሡዳን መሆኗ ይታወቃል።
ባለፉት አራት ወራት ግን ለሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ሃይል እንዳልቀረበ ነው የሰማነው።
የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በሀገሪቱ ያለው ግጭት እንደሆነ ተነግሯል።
ግጭቱ በሀገሪቱ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት በማስከተሉ የኤሌከትሪክ ሃይል ማቅረብ አልተቻለም ተብሏል።
ንጋቱ ረጋሣ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
Telegram : https://t.me/ShegerFMRadio102_1
Facebook፡ https://web.facebook.com/Sheger102.1








