top of page

በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ የላቁ የማህበረሰብ ስራ ፈጣሪዎችን እየመረጠ እውቅና የሚሰጠው የስኮል ወርልድ ፎረም በመጪው ሳምንት በእንግሊዝ ይደረጋል።

  • Apr 14
  • 2 min read

ሚያዝያ 6/2018


በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ የላቁ የማህበረሰብ ስራ ፈጣሪዎችን (social entrepreneurs) እየመረጠ እውቅና የሚሰጠው የስኮል ወርልድ ፎረም በመጪው ሳምንት በእንግሊዝ ኦክስፎርድ ይደረጋል።


በአካል ጉዳተኝነት አካታችነት ላይ በሰሩት የላቀ ስራ አቶ ገድለሚካኤል አበበ ከኢትዮጵያ እውቅናን ለማግኘት ከተመረጡት መሀከል መሆናቸው ተነግሯል።


የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ከላከልን መግለጫ እንዳየነው በዓመታዊው የስኮል ወርልድ ፎረም ላይ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ የተሰሩ ስራዎችን መርጦ የሚሸልመው ሚሲንግ ቢሊየን ኢኒሼቲቭ እውቅናን መስጠት ከጀመረ ሶስት ዓመት ሆኖታል።



በዘንድሮው የ2026 የስኮል ወርልድ ፎረም (Skoll World Forum) ከዓለም የላቁ የማህበረሰብ ስራ ፈጣሪዎች (social entrepreneurs) ስር በአካል ጉዳተኞች አካታችነት "ሚሲንግ ቢሊየን ኢኒሼቲቭ" ከተመረጡ ሰዎች ውስጥ የሆኑት አቶ ገድለሚካኤል በአካል ጉዳተኞች አካታችነት፣ ግንዛቤ እና የመርጃ መሳሪያዎችና ቴክኖሎጂዎች በማቅረብ ስራ ላይ የተሰማራው የብስራት ፕሮሞሽን ኃ.የተ.የግ.ማህበር መስራች መሆናቸው ተነግሯል።


የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ጋዜጠኞች ማህበርን ከመሰረቱት ጥቂት አካል ጉዳተኞች አንዱና በፕሬዝዳንትነት እየመሩ ያሉት አቶ ገድለሚካኤል በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን እና በሌሎችም አማራጮች የሚሰሯቸው አካል ጉዳተኞችን የተመለከቱ ዝግጅቶች በመላው ኢትዮጵያ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ጋር መድረስ ችለዋልም ብሏል መግለጫው።


አቶ ገድለሚካኤል አበበ በእንግሊዝ ኦክስፎርድ ከሚያዝያ 13 እስከ 16 ቀን 2018 ዓ.ም በሚካሄደው የዘንድሮ ጉባኤ ላይ ተገኝተው በኢትዮጵያ ስላለው አካል ጉዳተኞች እና የማህበረሰብ ስራ ፈጠራን የተመለከተ ልምዳቸውን ያጋራሉ ተብሏል።



በዚሁ ታላቅ ፎረም ላይም የአካል ጉዳተኞች እና አካታችነት አመራር ቡድን አባል በመሆን፣ ስለ አካል ጉዳተኞች ተደራሽነት፣ አጋዥ ቴክኖሎጂዎች፣ ሚዲያ እና አካታች ልማት የኢትዮጵያን ተሞክሮ እና ልምድ የተመለከተ ማብራሪያ ከህይወት ተሞክሯቸው በመነሳት በዝግጅቱ ላይ ያቀርባሉ።


ይህ አመታዊ ጉባኤ ከዓለም ዙሪያ ታዋቂና ታላላቅ ሰዎችን የሚያሰባስብ፣ከ100 በላይ ተናጋሪዎች የሚገኙበትና ከአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 2004 አንስቶ በየዓመቱ የሚካሄድ ነው።


ዓመታዊው የስኮል ጉባኤ(Skoll world forum)፣ ስኮል ፋውንዴሽን በተባለ ተቋም አዘጋጅነት በእንግሊዝ ኦክስፎርድ የሚካሄድ ነው።


ፋውንዴሽኑ በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 1999 ጄፍ ስኮል በተባለ አሜሪካዊ የተቋቋመ ሲሆን እኚህ ሰው የዓለም አቀፉ ታዋቂ የዲጂታል ገበያ መድረክ ኢቤይ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ናቸው።


ከዚህ ቀደም በዚህ ዓለም አቀፍ ፎረም ላይ በመገኘት ንግግር ካደረጉና ሀሳባቸውን ካጋሩ ታዋቂ ሰዎች መሀከል ኮፊ አናን፣ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ፣ ጂሚ ካርተር እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።


በዘንድሮው የ2026 ዝግጅት ላይም ዓለም አቀፍ ታዋቂ ግለሰቦች ይታደማሉ፣ንግግርም ያደርጋሉ ተብሏል።


ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ….

ቴዎድሮስ ወርቁ

1 Comment


Hany Macron
Hany Macron
Apr 22

The variety of tools and weapons available in the Melon playground game allows for endless creativity. I especially enjoy testing different combinations to see unexpected results.

Like
Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page