በወንጀል ተከሰው ጥፋተኛ ተብለው ከተቀጡት ውስጥ አብዛኞቹ በተደጋጋሚ ወንጀል በመስራት እንደሚቀጡ አንድ ጥናት ጠቆመ።
- 3 hours ago
- 2 min read
ሐምሌ 30 2018
በወንጀል ተከሰው ጥፋተኛ ተብለው ከተቀጡት ውስጥ አብዛኞቹ በተደጋጋሚ ወንጀል በመስራት እንደሚቀጡ አንድ ጥናት ጠቆመ።
ታራሚዎች ተከሰው የታሰሩበት አዲስ ወንጀል ከ53 በመቶ በላዩ በስርቆት ወንጀል የተሳተፉ እንደሆኑም ጥናቱ አሳይቷል፡፡
ታራሚዎች ተቀጥተው ከወጡ በኋላ ተመልሰው ወደ ሌላ ወንጀል የሚገቡበት ምክንያት ከማረሚያ ቤት ከወጡ በኋላ ሥራ ማግኘት አለመቻል፣ የገንዘብ ችግር እና ክትትልና ድጋፍ አለመኖር ተጠቅሰዋል።
ጥናቱን ያቀረቡት የፌዴራል ሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ሕግ ተመራማሪ የሆኑት ወ/ሪት ፍሬህይወት ግዛቸው ሲሆኑ፣ የጥናቱ ግኝት የቀረበው ኢንስቲትዩቱ ባዘጋጀው ዓመታዊ የሕግና የፍትሕ ጥናትና ምርምር ውጤቶች ላይ በነበረ የውይይት መድረክ ነው።
በጥናቱ በወንጀል ተከሰው የተቀጡ ታራሚዎች 57.9 በመቶ የሚሆኑት አንድ ጊዜ ፣31 በመቶ ሁለት ጊዜ የተቀሩት 8.7 በመቶ ሶስት ጊዜ፣ እንዲሁም 4 ጊዜ ቀደም ሲል በሌላ ተደጋጋሚ ወንጀል ተከሰው የተቀጡ መሆናቸውን ሰምተናል።
በወንጀል ተከሰው ቅጣት ተወስኖባቸው ውሳኔያቸውን ጨርሰው ከወጡ በኋላ 36 በመቶው ከሁለት እስከ 5 አመት ባለው በድጋሚ በሌላ ወንጀል የሚያዙ ናቸው ተብሏል፡፡
ነገር ግን የተደራጀና የተስተካከለ የመረጃ ሥርዓት ባለመኖሩ የኢትዮጵያን የተደጋጋሚ የወንጀል ምጣኔ ምን ያህል እንደሆነ ማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው ተብሏል።
ታራሚዎቹ ቀደም ሲል የፈጸሙት ወንጀል 52 በመቶ ዝርፊያ ወይም ስርቆት ሲሆን ቀሪዎቹ በጠብ ፣ በማታለል ፣ በግብር ሰወራና በማጭበርበር ፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የሙስና ወንጀሎችና ሌሎች ወንጀሎች ይገኙበታል።
የወንጀል ተደጋጋሚነት ምጣኔያቸው ዝቅተኛ የሆኑት እንደ ኖርዌይ፣ ሲንጋፖር እና ደቡብ ኮሪያ ከመሰሉ ሀገራት ተሞክሮ መውሰድ ፣ ተደጋጋሚ ወንጀል የሚሠሩት ነጥለው ለብቻ የሚያዙበት ራሱን የቻለ የማረም አሰራር መዘርጋት ፣ የወንጀል ቅጣት መጠንን መፈተሽና የሚስተካከሉትን ማሻሻል ፣ ታርመው ሲወጡ የሥራ ዕድል ማመቻቸት እና የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠት የተደጋጋሚ ወንጀልን ምጣኔ ለመቀነስ የሚያግዙ ምክረ-ሐሳቦች ሆነው በጥናቱ ተካተዋል።
ተደጋጋሚ ታራሚዎች ቀደም ሲል እና አሁን አዲስ የፈጸሙትና የተቀጡበት ወንጀል ከከባድ እስከ ቀላል ወንጀሎች ሲሆን ዋና ዋናዎቹ ግን ስርቆት ፣ ውንብድና፣ ማታለል ፣ ደረቅ ቼክ ፣ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀምና ማዘዋወር ፣ ሀሰተኛ ሰነድ እንዲሁም ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና አስገድዶ መድፈር በብዛት ተጠቅሰዋል።
ገዛ ጌታሁን
_edited.jpg)
