top of page

በኢትዮጵያ ወጥ የሆነ ሕጋዊ ማዕቀፍ ሳይበጀለት ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የተፋጠነ የወንጀል ፍርድ ሂደት (RTD)፣ ፍትሕን ከማረጋገጥ ይልቅ ለቅልጥፍና ቅድሚያ በመስጠቱ የዜጎችን ሕገ-መንግሥታዊ መብቶች ለአደጋ ማጋለጡ በጥናት ተጠቆመ።

  • 2 hours ago
  • 2 min read

ሐምሌ 30 2018


በኢትዮጵያ ወጥ የሆነ ሕጋዊ ማዕቀፍ ሳይበጀለት ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የተፋጠነ የወንጀል ፍርድ ሂደት (RTD)፣ ፍትሕን ከማረጋገጥ ይልቅ ለቅልጥፍና ቅድሚያ በመስጠቱ የዜጎችን ሕገ-መንግሥታዊ መብቶች ለአደጋ ማጋለጡ በጥናት ተጠቆመ።


ይህ አሠራር ግልጽ ማዕቀፍ የሌለው በመሆኑ በዳኝነትና በፍትሕ አካላት ግላዊ ውሳኔ ላይ የተመሠረተና የማይገመት እንዲሆን አድርጎታል ተብሏል።


ይህም በፌዴራልና በክልል ፍርድ ቤቶች መካከል በሚታዩ የወንጀል ዓይነቶችና የጊዜ ገደብ አተረጓጎም ላይ ከፍተኛ አለመጣጣም የፈጠረ ሲሆን፤ የተከሳሾችን ንጹሕ ሆኖ የመገመት፣ የመሰማት፣ የመከላከል፣ የሕግ ድጋፍ (ጠበቃ) የማግኘትና በዋስ የመፈታት ሕገ-መንግሥታዊ መብቶችንም አደጋ ላይ መጣሉ ተነግሯል።


የተፋጠነ የወንጀል ፍርድ ሂደት አተገባበር በአገሪቱ ውስጥ ወጥ የሆነ ሕጋዊ ማዕቀፍ የሌለው ሲሆን፤ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ ውስጥም አለመደንገጉ ተጠቁሟል።


ይህ የተባለው በፌዴራል ሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ዓመታዊ የሕግና ፍትሕ ጥናትና ምርምር ውጤቶች ላይ በተዘጋጀው የባለድርሻ አካላት የውይይትና የማረጋገጥ አውደ ጥናት ላይ ነው።


በፌዴራል ፍርድ ቤቶች (በአዲስ አበባ) እንዲሁም በክልል ፍርድ ቤቶች (በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች) ተካሄደ በተባለው ጥናት፣ በ2017 ዓ.ም በተፋጠነ ችሎት ውሳኔ ያገኙ 712 መዝገቦች ምርመራ ተደርጎባቸዋል ተብሏል።


ጥናቱን ያቀረቡት የፌዴራል ሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት የሕግ ተመራማሪ አቶ ኖህ ግርማ፤ ምርመራ ከተደረገባቸው 712 መዝገቦች መካከል 53.1 በመቶ የሚሆኑት በ30 ቀናት ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኙ ሲሆን፣ 66.9 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በሁለት ወር ውስጥ መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።


ከታዩት መዝገቦች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ተከሳሾች ያለ ጠበቃ ድጋፍ በሂደቱ ያለፉ ሲሆን፣ የራሳቸውን የመከላከያ ማስረጃ ማቅረብ የቻሉት 31.2 በመቶ ያህሉ ብቻ ስለመሆናቸውም በጥናት መረጋገጡን አቶ ኖህ አንስተዋል።


የተፋጠነ የወንጀል ፍርድ ሂደት በዋናነት ቀላል ወንጀሎችን ማስተናገድ ዓላማ ያደረገ ቢሆንም፣ በተግባር ግን እንደ ነፍስ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር እና ከባድ የአካል ጉዳት ያሉ ከበድ ያሉ የወንጀል መዝገቦች በተፋጠነ አሠራር መታየታቸው በጥናቱ ተመላክቷል።


ግልጽ መመሪያ ባለመኖሩ ምክንያት ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትና የአእምሮ ሕመምተኞችም በዚህ ሂደት ተካተው መገኘታቸው ተጠቅሷል።


በተለይም ተከሳሾች የቋንቋ አስተርጓሚ ሳያገኙ እና የክሱን ጭብጥ በበቂ ሁኔታ ሳይረዱ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ተደርጓል ተብሏል።


በተጨማሪም ወጥ የሆነ ሕጋዊ ማዕቀፍ አለመኖሩ የሕግ አስከባሪ አካላት ተከሳሾችን ለማስፈራራትና ለሙስና ተጋላጭ የሚሆኑበትን አጋጣሚ መፍጠሩ በጥናቱ መታየቱን የሕግ ተመራማሪው አቶ ኖኅ ግርማ አብራርተዋል።


የተፋጠነ የወንጀል ፍርድ ሂደትን የሚመራ ወጥ ሕጋዊ የአሠራር ማዕቀፍ መዘርጋት፣ ለዚሁ አሠራር ራሳቸውን የቻሉ ችሎቶችን ማዘጋጀት፣ የፍርድ ሂደቱን በቴክኖሎጂ ማገዝ፣ እና ለተከሳሽና ለተከላካይ ጠበቃ በቂ የመከላከያ ጊዜ መስጠት የሚሉት በጥናቱ በምክረ-ሐሳብነት ከተጠቀሱት መካከል ይገኙበታል።


ፈጣን የወንጀል ችሎት አሠራር ከፈረንሳይ በተወሰደ ተሞክሮ በኢትዮጵያ ተግባራዊ መሆን የጀመረው በ2000 ዓ.ም ነው።


አሠራሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የተደረገውም በሚሊኒየም በዓል አከባበር እና በቁልቢ ገብርኤል ንግሥ በዓል ወቅት እንደነበር ተነግሯል።


ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ...



ገዛ ጌታሁን

Recent Posts

See All
የሐምሌ 30 2018 የውጪ ሀገር ወሬዎች

#አራን ኢራን በአሜሪካ አዲስ ጥቃት የሚከፈትብኝ ከሆነ እኔም የባህረ ሰላጤውን የአሜሪካ ተባባሪዎች አልለቃቸውም ማለቷ ተሰማ፡፡ ቴሕራን በአሜሪካ ዳግም ጥቃት የሚሰነዘርብኝ ከሆነ እኔም የባህረ ሰላጤውን አገሮች የነዳጅ አውታሮች እንዳልነበሩ አድርጌ አወድማቸዋለሁ ማለቷን የፃፈው ሬውተርስ ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በስም

 
 
 
ኢትዮጵያውያኑ በዚህ መንገድ የሚጠለፉት አንዴት ነው?

ሐምሌ 30 2018 በኦንላይን የሚሰራ የእንግሊዘኛ ቋንቋና የኮምፒውተር እውቀት ያለው ደመወዝ በወር 1ሺህ ዶላር በሚሉ ማስታወቂያዎች ተታለው እንደ ማይናማር የመሳሰሉ የደቡብ ምስራቅ ኤዥያ አገራት የሄዱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ብዙ መከራ ፣ ግፍ አይተዋል፡፡ እድል የቀናቸው ለሀገራቸው በቅተዋል፡፡ ግን ኢትዮ

 
 
 
በመጪው ዓመት ከአዲስ አበባ ከተማ ግብር ከፋዮች 380 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ውጥን መያዙን የከተማዋ ገቢዎች ቢሮ ተናገረ።

ሐምሌ 29 2018 በመጪው ዓመት ከአዲስ አበባ ከተማ ግብር ከፋዮች 380 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ውጥን መያዙን የከተማዋ ገቢዎች ቢሮ ተናገረ። በ2019 በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ በአጠቃላይ 502.2 ቢሊዮን ብር ይሰበሰባል የተባለ ሲሆን ከዚህም ውስጥ የገቢዎች ቢሮ ድርሻ 380 ቢሊዮን ብር መሆኑን ቢሮ

 
 
 
Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page