''በክልሉ ያሉ ሰራተኞች ተንቀሳቅሶ ለመስራት በስጋት ውስጥ ናቸው'' የአማራ ክልል ቀይ መስቀል ማህበር
- sheger1021fm
- 10 minutes ago
- 1 min read
በቅርቡ የአማራ ክልል ቀይ መስቀል ማህበር ሰራተኛ በታጣቂዎች መገደሉን ተከትሎ ሌሎች በክልሉ ያሉ ሰራተኞች ተንቀሳቅሶ ለመስራት በስጋት ውስጥ ናቸው ተባለ።
የቀይ መስቀል ማህበር የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ተንቀሳቅሶ ለመስራት የማይቻልባቸው ያላቸውን ቦታዎች በጥናት መለየቱንም ተናግሯል።
በጥናቱ በተለዩት ቦታዎች የተሻለ ሰላም ካልመጣ ሰራተኞቼን ለመላክ እቼገራለሁ ብሏል።
ማህበሩ በቅርቡ በክልሉ የ #ቀይ_መስቀል ማህበር ሰራተኛ በታጣቂዎች መገደሉን ተከትሎ የማህበሩ አባላትና ሰራተኞች በአካባቢው ተንቀሳቅሰው ለመስራት ፈቃደኛ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋልም ብሏል።
ማህበሩ በአባላት ላይ የሚፈጸሙው እገታና ግድያ ሰብአዊ ድጋፍ ለሚሹ ሰዎች ለመድረስ እንቅፋት እንደሆነበትም ተናግሯል።
የቀይ መስቀል ማህበር የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሻምበል ዋለ ነሐሴ 7 ቀን በማህበሩ አባላት ላይ የተፈጸመው እገታ እና ግድያ በአባላቱ ላይ ከፍተኛ መደናገጥን ፈጥሯል ብለዋል።
በዚህም ሰራተኞቹ ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው ለመስራት ስጋት ላይ ጥሏቸዋልም ብለዋል።
የፀጥታ ሁኔታው አስጊ የሆነባቸውን ቦታዎች በጥናት ለይተናል ሲሉም ጠቁመዋል።
በተለይ በጎንደር መስመር የጸጥታ ስጋት እንዳለም ነግረውናል።
ለጊዜውም በአካባቢው እንቅስቃሴ እንዳይኖር ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር እየመከርንበት ነው ብለዋል።
በክልሉ በፀጥታ ችግር ምክንያት ለአባላቶች እና ለሰራተኞች ስጋት ናቸው ያልናቸውን ቦታዎች በጥናት ለይተን ጥናቱን ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ልከናል ያሉን አቶ ሻምበል ጥናታችን ተቀባይነት ካገኘ የእንቅስቃሴ ገደብ የጣልንባቸው አካባቢዎች አስተማማኝ የሰላም ሁኔታ ሲፈጠር እንቅስቃሴዎች ሊጀመሩ እንደሚችሉም በጥናቱ አንስተናል ብለዋል።
የቀይ መስቀል ማህበር የአማራ ክልል ቅርንጫፍ የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦትን ለመከወን ከፀጥታ ችግር ባለፈ የገንዘብ እጥረት እንዳለበትም ተናግሯል።
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ...
ፍቅሩ አምባቸው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s