''በኢትዮጵያ የሚካሄደው የጣሊያን የምግብ ሳምንት የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ይበልጥ እንዲጠናከር እያደረገ ነው'' የጣሊያን ኤምባሲ
- sheger1021fm
- Dec 2
- 1 min read
ህዳር 23 2018
በኢትዮጵያ የሚካሄደው የጣሊያን የምግብ ሳምንት የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ይበልጥ እንዲጠናከር እያደረገ ነው ሲል አዲስ አበባ የሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲ ተናገረ፡፡
ለ4 ቀናት የተካሄደው የጣሊያን የምግብ ሳምንት መጠናቀቁንም ሰምተናል፡፡
ዝግጅቱን የጣሊያን የንግድ ኤጀንሲ በኢትዮጵያ ከሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን ሲካሄድም ለ10ኛ ጊዜ ነው፡፡

የጣሊያን የምግብ ዝግጅት ሣምንት የጣሊያን የምግብ ባህል ያስተዋወቀ እንዲሁም ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ወዳጅነት ያሳየ ሆኖ ተጠናቋል ሲሉ በአዲስ አበባ የጣሊያን ንግድ ኤጀንሲ የንግድ ኮሚሽነር ክላውዲዮ ፓስኳሉቺ ተናግረዋል፡፡
‘’የጣሊያን ሼፎችን ከኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እና ተማሪዎች ጋር በማገናኘት የባህል ዲፕሎማሲውን እንዲጠናከር አድርገናል እንዲሁም በምግብ ጥናት እና ዝግጅት ዘርፍ አዳዲስ የትብብር ዕድሎችን ከፍተናል" ሲሉም አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ውስጥ እንግዶች፣ ተማሪዎች በተገኙበት የጣሊያንን ባህላዊ እና ዘመናዊ ምግቦች የማጣጣም ዝግጅት መካሄዱንም ሰምተናል፡፡
ጣሊያናዊው ሼፍ ኤልያ ግሪሎቲ ኢትዮጵያውያን ሼፎች እና የምግብ ዝግጅት ተማሪዎች ስለ ምግብ ዝግጀት የተግባር ስልጠናዎችን እና ማሳያዎችን ማቅረቡም ተጠቅሷል።
በአጠቃላይ ባለፉት አራት ቀናት የተካሄዱት ፕሮግራሞች የጣሊያንን የምግብ አሰራር አሳይተዋል፣ በዚህም በኢትዮጵያ እና በጣሊያን መካከል በመስተንግዶ ዘርፍ ለልምድ ልውውጥ በር እንዲከፈት ያበረታታ ሆኖ አልፏል ሲሉ የጣሊያን ንግድ ኤጀንሲ የንግድ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

ምግብ እንዴት ማህበረሰቦችን አንድ እንደሚያደርግ፣ ትብብርን እንደሚያበረታታ እና የጋራ መግባባትን እንደሚያጎለብት የምግብ ዝግጅት ሳምንቱ አሳይቷል ተብሎለታል፡፡
የጣሊያን ምግብ ሳምንት በጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በጣሊያን ንግድ ኤጀንሲ የተዋወቀው ዓለም አቀፍ ተነሳሽነት ሲሆን ዓላማውም የጣሊያንን የምግብ አሰራር ለባህል ዲፕሎማሲ እና የምግብ ዘርፍ ወጪ ንግድን ማበረታታት ነው፡፡
ንጋቱ ሙሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp https://tinyurl.com/ycxjmm3s











Comments