top of page

በኢትዮጵያ እስካሁን በረቂቅ ደረጃ ያለውና የታሸጉና በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን የሚቆጣጠር ህግ

  • 55 minutes ago
  • 2 min read

ሐምሌ 14/2018


በኢትዮጵያ እስካሁን በረቂቅ ደረጃ ያለውና የታሸጉና በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን የሚቆጣጠር ህግ ፈጥኖ ሥራ ላይ ካልዋለ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚደርሰው የጤና ጉዳት እየተባባሰ ለመከላከል የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ መሆኑ አይቀርም ተባለ።


አሁንም ኢትዮጵያ ተላላፊ ባልሆኑ ህመሞች ምክንያት ለሚመጡ የጤና ችግሮች በየአመቱ 31 ቢሊየን ብር ታወጣለች ተብሏል።


የስኳር፣ የጨውና የቅባት መጠናቸው ከፍተኛ እንዲሁም በፋብሪካ የተቀነባበሩ የታሸጉ ምግቦችን ለመቆጣጠር የተዘጋጀው ረቂቅ ህግ በፍጥነት ሥራ ላይ ካልዋለ በህብረተሰቡ ጤና ላይ የሚደርሰው ጉዳት እየጨመረ እንደሚሄድ ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።


በዚሁ ጉዳይ ላይ ዛሬ ማቴዎስ ወንዱ ፋውንዴሽን ከመንግሥት ተቋማት፣ ከጤና ባለሙያዎች፣ ከሲቪል ማኅበራት፣ ከሸማቾች ተወካዮች እና ሌሎች ከሚመለከታቸው ጋር ባሰናዳው ምክክር ላይ ነው ይህ የተባለው ።


በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦች በህብረተሰቡ ጤና፣ በተለይም በህጻናትና በወጣቶች ላይ እያስከተሉ ስላለው ተፅዕኖዎች ውይይት ተደርጓል።


በተለይ ለህጻናትና ለወጣቶች በስፋት የሚቀርቡ ጣፋጭ መጠጦች፣ የታሸጉ እና ሌሎች በፍጥነት የተዘጋጁ ምግቦች ከመጠን በላይ መጠቀም ከመጠን ላይ ውፍረት፣ ለስኳር በሽታ፣ ለደም ግፊት፣ ለልብና ደም ሥር በሽታዎች እንዲሁም ለሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭነትን በፍጥነት እየጨመረ መሆኑ ተነግሯል።


በመሆኑም በምግቦቹ ላይ የንጥረ ነገር መጠንን በግልጽ የሚያሳይ መለያ፣ ለህጻናት የሚቀርብ ማስታወቂያ ላይ ገደብ፣ እንዲሁም ከፍተኛ የስኳር፣ የጨውና የቅባት መጠን ያላቸውን ምግቦች ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን የያዘው ረቂቅ ህግ በቶሎ መጽደቅ እንዳለበት ጥሪ ቀርቧል።


በተጨማሪም የህጉ መዘግየት ጤናማ የምግብ ልምድን ከማበረታታት ይልቅ ጎጂ ምግቦች በገበያ ላይ ያለ በቂ ቁጥጥር እንዲቀጥሉ በማድረግ በረጅም ጊዜ የህክምና ወጪን እንዲጨምርና በሀገሪቱ የጤና ሥርዓት ላይ ተጨማሪ ጫና የሚፈጥር ነው ተብሏል።


በተለይም በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በማኅበራዊ ሚዲያና በሌሎች ዲጂታል መድረኮች የሚቀርቡ ሳቢና አማላይ ማስታወቂያዎች ህጻናትና ወጣቶች እነዚህን ምርቶች እንዲመርጡ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደሩ መሆኑ ተነስቷል።


በመሆኑም ህጻናት ላይ ትኩረት ያደረጉ የእነዚህ ምርቶች ማስታወቂያዎች በህግ እንዲገደቡ ለማድረግ የህጉ መኖር አስተዋጽኦ እንዳለው ተነግሯል።


በምግቦች ፊት ለፊት የንጥረ ነገር ይዘትን በግልጽ የሚያሳይ መለያ ማድረግ፣ ለህጻናት የሚቀርቡ ማስታወቂያዎችን መቆጣጠር፣ እንዲሁም ጤናማ የምግብ አማራጮችን ማበረታታት በህብረተሰቡ ጤና ላይ የሚታየውን ጫና ለመቀነስ አስፈላጊ እርምጃዎች መሆናቸው ተጠቅሷል።


በፋብሪካ የተቀነባበሩ እና በጊዜ ሂደት ለተለያዩ ተላላፊ ላልሆኑ ህመሞች የሚያጋልጡ ምግቦችን ለመቆጣጠር የተዘጋጀው ረቂቅ ህግ በፍጥነት ጸድቆ ወደ ተግባር እንዲገባ፣ ይህም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመቀነስና የህብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ባለሙያዎቹ አሳስበዋል።


በዓለም ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶችና የጤና ፖሊሲዎች በፋብሪካ የተቀነባበሩና በስኳር፣ በጨው እና በቅባት የበለጸጉ ምግቦችን ለመቆጣጠር ቀድመው ሕግ ያወጡ ሀገራት በህብረተሰቡ የምግብ ምርጫ እና በህጻናትና ታዳጊዎቻቸው የጤና ሁኔታ ላይ የተሻለ ውጤት እያሳዩ ነው ተብሏል።


ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ለስኳር ፣ ለልብ ፣ ለደም ግፊት፣ ለስትሮክ እና ለአንዳንድ ካንሰሮች ዋነኛ አጋላጭ መንስኤ ሲሆን በየዓመቱ በአለም ዙሪያ 8 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ጤናማ ባልሆነ የአመጋገብ ችግር ምክንያት ሕይወታቸውን ያጣሉ።


በተጨማሪ የሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በእነዚህ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ተጎድተው ለረጅም ጊዜ ህክምና በመፈለጋቸው ችግሩ በሀገራት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መሆኑ ተነግሯል።


ምህረት ስዩም

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page