በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ግብአትን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች እንደተፈቱላቸው ተነግሯል፡፡
- 2 hours ago
- 2 min read
ሰኔ 9/2018
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ግብአትን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች እንደተፈቱላቸው ተነግሯል፡፡
በሌላ በኩል ዛሬም ግብአቶች ከውጪ የሚያስገቡ አምራች ኢንዱስትሪዎች አሉ ተብሏል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ስራ ያቆሙ ፋብሪካዎች ወደ ማምረት እንዲመለሱ ማስቻል እንደሆነ ይነሳል።
ያሉባቸው የመሬት፤ የብድር፤ የመሠረተ ልማትና የግብአት አቅርቦት ችግሮች ተፈትተውላቸው 800 የሚሆኑ ፋብሪካዎች ወደ ምርት መመለሳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ሚያዝያ ወር ተናግረዋል።
አንዳንድ ፋብሪካዎች ስራ ባያቆሙም የማምረት አቅማቸው በጣም ዝቅተኛ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ በዚህ ንቅናቄ የፋብሪካዎቹ የማምረት አቅም ከ47 በመቶ ብቻ ወደ 67 በመቶ እንዲያድግ መደረጉን አመልክተዋል።
ከውጭ ይገባ የነበረን እና ከ3 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ ግምት ያለው ምርት በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏልም ብለዋል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ይፋ ባደረገው ጥናቱ ደግሞ አምራች ኢንዱስትሪዎች ግብአቶችን ከሀገር ውስጥ ለማግኘት አሁንም እየተቸገሩ እንደሆነ አመልክቷል።
እንደ ኢንስቲትዩቱ መረጃ ኢንዱስትሪዎቹ ግብአቶቹን በበቂ መጠን እና ጥራት ከሀገር ውስጥ ማግኘት እየቻሉ ስላልሆነ ከውጪ እያስገቡ ነው።
በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያሉ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራች ኢንዱስትሪዎች ጥጥ ሳይቀር ከውጪ ለማምጣት መገደዳቸውን ጥናቱ ይጠቅሳል።
አምራች ኢንዱስትሪዎች ግብአትን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮቻቸው እየተፈቱላቸው ነው ከተባለ እንዴት አሁንም ከውጪ ያስገባሉ? ስንል ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርበናል።
ለጥያቄያችን ምላሽ የሰጡን ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት እና የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ አበባ ታመነ ፤ የግብአት ችግሩ እየተፈታ ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ በሚሸፈንበት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት እንዳልሆነ ነግረውናል።
ብዛት ያለው ግብአት ፤ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ በሀገር ውስጥ እንዲመረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው እየሰራ እንደሚገኝ የነገሩን ስራ አስፈጻሚዋ ማበረታቻዎች ጭምር እንደሚደረጉ አክለዋል፡፡
ለኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልጉ ግብአቶች ከተለያዩ ዘርፎች የሚገኙ እንደሆነ ያስታወሱት ስራ አስፈጻሚዋ ፤ ሁሉም በየመስኩ እነዚህ ግብአቶች ጥራታቻውን ጠብቀው በበቂ መጠን እንዲመረቱ የማስተባበሩን ሃላፊነት እንዲወጣ በጋራ እየሰራን ነው ብለውናል፡፡
ከውጪ የሚገቡ 96 ምርቶችን እዚሁ የሚገኙ ግብአቶችን በመጠቀም በሀገር ውስጥ መተካት እንደሚቻል በጥናት መረጋገጡ የጠቀሱት ወይዘሮ አበባ ፤ ቀስ በቀስ ወደ ስራ እናስገባቸዋለን ብለዋል፡፡
ከስምንት ዓመት በፊት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢንዱስትሪ ግብዓት ከውጪ የሚገባ እንደነበር ተጠቅሷል።
ይህንን ለማስቀረት በርካታ ሥራዎች እንደተሰሩ ስራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ…
ንጋቱ ረጋሣ





Comments