top of page

በኢትዮጵያ በተፈጥሯዊው የወር አበባ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ከስራቸው የሚስተጓጎሉ ሴቶች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡

  • 2 hours ago
  • 2 min read

ሰኔ 8/2018


በኢትዮጵያ በተፈጥሯዊው የወር አበባ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ከስራቸው የሚስተጓጎሉ ሴቶች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡


በወር አበባ ምክንያት ከሚፈጠርባቸው ህመም በተጨማሪ ግን እለት ከለት እየናረ የመጣው የንጽህና መጠበቂያ ሞዴስ ዋጋ አሳሳቢ ሆኗል፡፡


በተለይ ዝቅተኛ የገቢ መጠን ያላቸው እንደ ኢንደስትሪ ፕርኮች ባሉ ቦታዎች ላይ የሚሰሩ ሴቶች በዚህ እየተቸገሩ መሆኑን ይናገራሉ፡፡


የወር አበባ ጤና ቀንን አስመልክቶ ኤድስ ሄልዝ ኬር ፋውንዴሽን ወይም ኤ ኤች ኤፍ ኢትዮጵያ በአዳማ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ባሰናዳው ዝግጅት ላይ ተገኝተን እንደሰማነው በንጽህና መጠበቂያ እጥረት ምክንያት 46 ከመቶ ሴቶች ከትምህርት ቤት ይቀራሉ፡፡



በሌላ በኩል በስራቸው ምክንያት ያልተመቸ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙና ህመም የሚገጥማቸው ሴቶችም በተፈጥሯቸው ሳቢያ ለብዙ ስቃይ እንደሚዳረጉም ተነግሯል፡፡


በተለይ የገቢ መጠናቸው አነስተኛ ለሆኑ ሴት ሰራተኞች የንጽህና መጠበቂያ እንደልብ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን በአዳማ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የጤና ክፍል አስተባባሪ የሆኑት አቶ አለማየሁ ጋረደው ይናገራሉ፡፡


ከዚህ ቀደም በኢኮኖሚ ዞኑ ለሚሰሩ ሴት ሰራተኞች ከዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማት ጋር በመሆን የንጽህና መጠበቂያዎችን በዝቅተኛ ዋጋ እንዲያገኙ ሲሰራ ነበር አሁን ግን ያ በመቋረጡ እየተቸገሩ ነው ነገር ግን ሌሎች ከህመም ጋር የተያያዙ እንዲሁም ለንጽህና መጠበቂያ የሚሆን ቦታዎችን በማመቻቸት ግን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡


በወር አበባ ላይ ያለው የአንዳንድ ማህበረሰብ አመለካከት ዝቅተኛ መሆኑ ሴቶች በተፈጥሯቸው ጉዳይ ምክንያት ጫና እንዲበዛባቸው አድርጓል ይንን ለማስተካከል የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች ተጀምሯል የሚሉት ደግሞ በጤና ሚኒስቴር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ወይዘሮ ፋጡማ ሰይድ ናቸው፡፡



በየጊዜው ዋጋው እየናረ የመጣው የንጽህና መጠበቂያ ተደራሽ እንዳይሆን ከቀረጥና ሌሎች የፖሊሲ ማሻሻያዎች ጋር በተያያዘ ለብዙ አመታት ሲወራ ቢቆይም አሁንም ድረስ መፍትሄ አልተሰጠውምና እዚህ ላይ ግፊት በማድረግ በኩል የጤና ሚኒስቴር ምን እየሰራ ነው ያልናቸው ወይዘሮ ፋጡማ የዋጋውን ጉዳይ በተመለከተ በመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት በጋራ በመሆን የመግዛት አቅም ለሌላቸው ሴቶች አቅርቦቶች እንዲበዙ በነፃ የሚሰጥበት ወይም ደግሞ በትንሽ ዋጋ እንዲቀርቡ የሚደረግበት አሰራሮች ተዘግተዋል ብለዋል፡፡


ነገር ግን ይህም ቢሆን በቂ ባለመሆኑ በተለይ ከታክስ ጋር ያለውን ችግር ለማስተካከል ጤና ሚኒስተር ብቻውን ሳይሆን ከሌሎች ተቋማት ጋር ግፊት እያደረገ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡


በኢትዮጵያ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች 39 በመቶ የሚሆኑት ለሴቶች መሰረታዊ የንጽህና መጠበቂያ የሚሆኑ ቦታዎች ያልተሟሉላቸው መሆኑንና በተለይ በገጠር የሃገሪቱ ክፍል ከሚገኙ 75 በመቶ ልጃገረዶች በቂ የንጽህና መጠበቂያ እንደማያገኙ የዩኒሴፍ ሪፖርት ያሳያል፡፡


ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ….


ምህረት ስዩም


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page