በአርሲው ግጭት የ11 ሰዎች ህይወት ማለፉን ከዚህ ውስጥ 8ቱ የፀጥታ አካላት መሆናቸወን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡
- 10 hours ago
- 1 min read
ሰኔ 30/2018
በአርሲው ግጭት የ11 ሰዎች ህይወት ማለፉን ከዚህ ውስጥ 8ቱ የፀጥታ አካላት መሆናቸወን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡
በዚህ ግጭት 22 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ያሉ ሲሆን ከ90 በመቶ በላይ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለሳቸወን አስረድተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ይህንን ያሉት የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጡ ባለበት ወቅት ነው።

ከሃይማኖት ግጭቶች ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ በቅርቡ በአርሲ የነበረውን ግጭት አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአርሲው ግጭት ምርጫውን ለማደናቀፍ ጥረት ሲያደርጉ ነበር ያሏቸው ኃይሎች በአዲስ አበባ እና በምርጫ አከባቢ ከፍተኛ የፀጥታ ጥበቃ ሲደረግ ስለነበር ወደ አንድ መንደር ሄደው አርሲ ላይ ጥቃት ፈፅመዋል ብለዋል።
ምርጫውን ያደናቅፋሉ ያሏቸው ኃይሎች ለዚህ አላማቸው ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርጉ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአዲስ አበባ የዕምነት ተቋማት ሳይቀር ቦምብ እና ክላሽ ስንለቅም ነበር ብለዋል።
የአርሲው ግጭት ምርጫውን የማደናቀፍ እንጂ የሃይማኖት መልክ የላቸውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቅርቡ በሰራነው ጥናት ከ50 በመቶ በላይ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ባለባቸው ወረዳዎች ከ1000 በላይ ቤተክርስቲያን ተገንብተዋል ብለዋል።
ታዲያ ግጭቱ ሃይማኖታዊ ቢሆን ኖሮ ከዚህ ሁሉ ወረዳዎች ለምን በጥቂት ወረዳዎች ውስጥ ብቻ ሆነ? ሲሉ ጠይቀዋል።
አዲስ አበባ ተቀምጠው ጫት እየቃሙ ያለምንም መረጃ ግጭት የሚያራግቡ አካለት ጥንቃቄ አንዲያደርጉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስጠንቅቀዋል፡፡





Comments