top of page

በሽብር ወንጀል በተጠረጠሩት የኢሕአፓ አመራሮች እና አባላት ላይ ተጨማሪ 10 ቀን የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ፡፡

  • 1 day ago
  • 2 min read

ነሐሴ 11 2018


በሽብር ወንጀል በተጠረጠሩት የኢሕአፓ አመራሮች እና አባላት ላይ ተጨማሪ 10 ቀን የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ፡፡


​በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር በዋሉት የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) አመራሮችና አባላት ላይ መርማሪ ፖሊስ ያቀረበውን ጥያቄ በመቀበል፣ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ የ10 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።


​በዛሬው ዕለት ረፋድ 4:00 ሰዓት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የቀረቡት የኢሕአፓ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይስሐቅ ወልዳይ፣ የፓርቲው አባል አቶ አበበ አካሉ እና ጠበቃ አበራ ንጉሥ ናቸው።


​ቀደም ሲል በነበረው ችሎት ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ያደረጉትን ንግግር የድምፅ ቅጂ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረበ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱም ቅጂውን ካዳመጠ በኋላ «ለጥርጣሬ መነሻ የሚሆን መጠነኛ መረጃ አግኝቼበታለሁ» በማለት ለፖሊስ የ12 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዶ እንደነበር ይታወሳል።


​መርማሪ ፖሊስ በተፈቀደለት የ12 ቀን ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸውን ተግባራት ለችሎቱ ለአስረድቷል።


በዚህ መሠረት: ​ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የቴክኒክ መረጃዎችን መቀበሉን፤


​የፎረንሲክ ምርመራ ውጤቶችን በደብዳቤ መጠየቁን፤ እንዲሁም የአንድ የሰው ምስክር ቃል መቀበሉን ለችሎቱ አብራርቷል ።



በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ በአካል ተገኝተው «የመንግሥት የፀጥታ አካላት ሕዝብን እየጨፈጨፉና ንብረት እያወደሙ ስለሆነ ወጣቱ ተደራጅቶ፣ ሰልጥኖና ታጥቆ ራሱን እንዲከላከል» በማለት በሕገ-ወጥ መንገድ ሰዎችን ሲያደራጁ እንደነበር የቴክኒክ ማስረጃዎች ያስረዳሉ ብሏል።


​ፖሊስ አሁንም ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከመንግሥትና ከግል ባንኮች እንዲሁም ከብዙኃን መገናኛ ባለሥልጣን የሚቀበላቸው የሰነድና የቴክኒክ ማስረጃዎች ቀሪ መሆናቸውን ለችሎቱ አስረድቷል።


በመሆኑም ከወንጀሉ ውስብስብነትና አሳሳቢነት አንፃር የቀሩትን ማስረጃዎች አሰባስቦ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።


የተጠርጣሪዎች ጠበቆች ደንበኞቻቸው በቁጥጥር ስር የዋሉት በቂ የጥርጣሬ መነሻ ኖሮ ሳይሆን፣ አቶ አበበ አካሉና አቶ ይስሐቅ ወልዳይ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በመሆናቸው፤ ጠበቃ አበራ ንጉሥ ደግሞ የአቶ ታዬ ደንደኣ ጠበቃ በመሆናቸው ብቻ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።


​ፖሊስ በተፈቀደለት 12 ቀናት ውስጥ የአንድ ሰው ምስክር ቃል ከመስማትና ደብዳቤ ከመጻፍ ውጭ የሰራው አዲስ የምርመራ ሥራ አለመኖሩ ጉዳዩ በበቂ ጥርጣሬ ላይ ያልተመሠረተ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።


​ፖሊስ በዛሬው ዕለት «በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ አካባቢ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ሲያደራጁ ነበር» ሲል ያቀረበው ክስ አዲስና ቀደም ሲል ያልነበረ መሆኑንም ጠቅሰዋል።


​ማስረጃ ይገኛል የተባለባቸው ተቋማት የመንግሥት በመሆናቸው፣ ተጠርጣሪዎቹ በዋስትና ቢወጡ እንኳ የሚያጠፉት ማስረጃ እንደሌለ እንዲሁም በአዲስ አበባ ቋሚ አድራሻና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን በመግለጽ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።


​ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ ከሰዓት 9፡00 ሰዓት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።


ከሰዓት በኋላ ባዋለው ችሎትም ለፖሊስ ተጨማሪ የ10 ቀን የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ፣ ለነሐሴ 21 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።


ገዛ ጌታሁን

Recent Posts

See All
ተማሪዎች የሰው ሠራሽ አስተውህሎት (AI) አጠቃቀም ላይ ከመምህራኖቻቸው ቀድመው የሚገኙ ከሆነ በመማር ማስተማር ሂደት ላይ ክፍተት መፍጠሩ አንደማይቀር ተጠቆመ።

ነሐሴ 12 2018 ተማሪዎች የሰው ሠራሽ አስተውህሎት (AI) አጠቃቀም ላይ ከመምህራኖቻቸው ቀድመው የሚገኙ ከሆነ በመማር ማስተማር ሂደት ላይ ክፍተት መፍጠሩ አንደማይቀር ተጠቆመ። ችግሩን ለመቅረፍ መምህራንን በቴክኖሎጂው ማብቃትና AIን በራሱ እንደ አንድ የትምህርት ኮርስ አዋህዶ መስጠት እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ተመ

 
 
 
የነሐሴ 12 የውጪ ሀገር ወሬዎች

#ሩሲያ የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ብሪታንያን በብርቱ አስጠነቀቋት፡፡ ፑቲን ብሪታንያ ለዩክሬይን ግዛት ተሻጋሪ ድሮኖችን ከማቀበል ብትቆጠቢ ይሻልሻል ማለታቸው ሬውተርስ ፅፏል፡፡ ቀደም ሲል ታይምስ ጋዜጣ ዩክሬይን በሩሲያ ላይ ግዛት ተሻጋሪ ጥቃት የምታደርሰው በብሪታንያ ስሪት ድሮኖች እንደሆነ መዘገቡ ተጠቅሷ

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page