top of page

በምርጫ ወቅት ከህግ ውጪ የሆነ ተግባር የፈፀሙ የምርጫ አስፈፃሚዎችን ከስራ ማሰናበቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተናገረ።

  • 31 minutes ago
  • 1 min read

ግንቦት 25/2018


በምርጫ ወቅት ከህግ ውጪ የሆነ ተግባር የፈፀሙ የምርጫ አስፈፃሚዎችን ከስራ ማሰናበቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተናገረ።


የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ የምርጫውን እለትና የድምፅ ቆጠራ እየተካሄደበት ነው ያሉትን የዛሬውን እለት ክንውን በተመለከተ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ነው:።


የተለያዩ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ የቦርዱ የክትትል ቡድን ባደረገው አሰሳ ከህግ ውጪ የሆነ ተግባር ሲፈፅሙ የተገኙ ምርጫ አስፈፃሚዎች መገኘታቸውን ተናግረዋል።


አድርገውታል የተባለው  ህገ ወጥ ተግባር ባይፍታታም አዲስ አበባ ላይ ምርጫ ሲያስፈፅሙ የነበሩ ሁለት ሰራተኞች ናቸው ከስራ ተባርረዋል የተባለው።


በተያያዘም  ቡርጂ በተባለ የምርጫ ጣቢያ ትናንት የምርጫ አስፈፃሚዎች  የምርጫ ወረቀቱን ራሳቸው ሲሞሉ ተገኝተዋል በመባሉ ጣቢያው መዘጋቱን እና በስፍራው የተደረገው ምርጫም መሰረዙን ዋና ሰብሳቢዋ  ጠቅሰዋል፡፡

የድምፅ ቆጠራውን በተመለከተም እስከ ዛሬ ምሽት ድረስ በአዲስ አበባ ፣ በአማራ፣ በሶማሌ፣ በጋምቤላ እና በሲዳማ ክልል ገና ቆጠራ እየተካሄደባቸው ያሉ የምርጫ ጣቢያዎች አሉ ተብሏል።


ይህም በምርጫ ወቅት ረዥም ሰልፉ ስለነበር እና ተራዝሞ ከእኩለ ለሊት በኋላም ሲካሄድ የነበረ መሆኑን ተከትሎ የተከስተ መዘግየት ነው ብለዋል የምርጫ ቦርድ ስብሳቢዋ።


እንደ አጠቃላይ ሰባተኛው ሃገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ተካሂዷል ያሉት ወ/ሮ ሜላትወርቅ የድምፅ ውጤቱ ጊዜውን ጠብቆ በህጉ መሰረት ተጣርቶና አሸናፊው ወገን ተለይቶ ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።


በተጨማሪም በምርጫው ወቅት አጋጥመው ነበር ከተባሉ ችግሮች መካከል ሲቪል የለበሱ የመንግስት አስተዳደር አካላት በማይገባቸው የምርጫ ጣቢያ ክልል ገብተው መገኘታቸውን ቦርዱ በማረጋገጡ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መደረጉን ዋና ስብሰቢዋ በመግለጫቸው አካትተዋል፡፡


የፓርቲ ወኪሎችም በምርጫው ወቅት በታዛቢነት ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዳይገቡ የተከለከሉ እንደነበሩ አረጋግጠናል ያሉት ሰብሳቢዋ  ችግሩን ፈትተን በቆጠራው ወቅትም ጭምር እንዲሳተፉ አድርገናል ብለዋል።


የምርጫ ውጤቱ ቢያንስ በ10 ቀን ቢበዛ እስከ 20 ቀን ድረስ በቦርዱ ይፋ ይደረጋል ተብሏል።


ትዕግስት ዘሪሁን

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page