በ'ፊንቴክ' የማጭበርበር ወንጀል የተጠረጠሩ አርቲስቶች እና ቲክቶከሮች ላይ ፖሊስ የጠየቀው የተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ላይ ለመወሰን ፍርድ ቤት ለነገ ቀጥሯል።
- Apr 9
- 1 min read
ከ"ፊንቴክ" (Fintech) ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ በከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት አርቲስቶች እና ቲክቶከሮች ዛሬ መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
መርማሪ ፖሊስ በቀሪ የምርመራ ስራዎች ምክንያት ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል።
ባለፉት 12 የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት ለፍርድ ቤቱ ያስረዳው ፖሊስ፣
12 የመንግስት እና የግል ሚዲያዎች እንዲሁም ሁሉም የሀገሪቱ ባንኮች በጉዳዩ ዙሪያ ያላቸውን መረጃ በጽሁፍ እንዲልኩ መጠየቁን አስረድቷል።
እስካሁን የ150 ምስክሮችን ቃል የተቀበለ ሲሆን፣ ገና ያልተሰሙ ሌሎች ተጨማሪ ምስክሮች መኖራቸውን ጠቁሟል።
እያንዳንዱ ተጠርጣሪ በወንጀል ድርጊቱ ውስጥ የነበረውን የግል ተሳትፎ እና የጥቅም ትስስር የሚገልጽ ማብራሪያ ለችሎቱ አቅርቧል።
የተጀመሩ የሰነድ እና የሰው ማስረጃ ማሰባሰብ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲሰጠው ጠይቋል።
በተቃራኒው የተጠርጣሪዎች ጠበቆች ደንበኞቻቸው በዋስ እንዲፈቱ ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርበዋል።
ጠበቆቹ ባቀረቡት መከራከሪያ፦ ፖሊስ የጠቀሳቸው ቀሪ የምርመራ ስራዎች ተጠርጣሪዎቹ በውጭ ሆነው ሊከናወኑ የሚችሉ እንጂ የእነሱን መታሰር የግድ የማይሉ መሆናቸውን፤ ተጠርጣሪዎቹ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን እና የተወሰኑት ደግሞ የጤና እክል ያለባቸው መሆኑን በመጥቀስ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ፣ የፖሊስን የምርመራ መዝገብ መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለነገ ሚያዝያ 01 ቀን 2018 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ገዛ ጌታሁን





Comments