ሰኔ 9 2017 - የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የሚፈቅደው ረቂቅ ህግ ''ህገ መንግስቱን ይቃረናል'' የሚል ቅሬታ ከፓርላማው ቀረበበት
- sheger1021fm
- 10 hours ago
- 2 min read
የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ወይም ይዞታ ባለቤት እንዲሆኑ የሚፈቅደው ረቂቅ ህግ ''ህገ መንግስቱን ይቃረናል'' የሚል ቅሬታ ከፓርላማው የህግ ክፍል ቀረበበት፡፡
የፍትህ ሚኒስቴር በበኩሉ መሬትን በይዞታነት ወይም ደግሞ ቤትን ባለቤትነት መያዝ የሚከለክለው ህገ መንግስቱ ሳይሆን ፍትሐ ብሔር ነው ብሏል፡፡
በተጨማሪም ረቂቅ አዋጁ ''የካፒታል ሽሽትን ለያስከትል ይችላል ከኢትዮጵያዊያን ባህል፣ ወግ፣ እሴትና ሃይማኖት ጋር የሚቃረኑ ባህሎች ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ በር ከፋች ሊሆን ይችላል'' የሚል ትችትም ከምክር ቤት አባላት ቀርቦበታል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ላይ ይህ ቅሬታ የቀረበበት የከተማ፣ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በረቂቅ አዋጁ ላይ ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡
በውይይቱ ላይ ከህግ ጉዳዮች ጥናት ዳይክቶሬት የተዘጋጁትን ጥያቄዎች በንባብ ያቀረቡት ወ/ሪት አለምፀሀይ ይመች ''ከሀገሪቱ ህጎች ሁሉ የበላይ በሆነው ህገ መንግስት አንቀጽ 40 ንዑስ ቁጥር 3 የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት ባለቤትነት መብት የመንግስት እና የህዝብ ብቻ እንደሆነ ይገልጻል'' ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ''በዚሁ አንቀጽ 40 ንዑስ ቁጥር 6 መሰረት መንግስት ለግል ባለሀብቶች በክፍያ ከመሬት የመጠቀም መብትን የሰጠው ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ወይም ደግሞ ለውጭ አልሚዎች ነው እንጂ ለማንኛውም የውጭ ዜጎች አይደለም፤ ለዚህም ማብራርያ ቢሰጥበት?'' ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥያቄዎችን በንባብ ያቀረቡት የምክር ቤት አባል በበኩላቸው ''በህገ በመንግስቱ አንቀጽ 40 ንዑስ ቁጥር 6 ላይ የመሬት ባለቤትነት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች መሆኑን እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስት ለግል ባለሃብቶች በህግ በሚወሰን ክፍያ በመሬት የመጠቀም መብታቸውን ያስከብርላቸዋል'' እንደሚልም ጠቅሰዋል፡፡
''ነገር ግን ስለ ውጭ ዜጎች መብት የሚገልጽ በሌለበት እንዴት የውጭ ሀገር ዜጎችን ባለመብት እንዲሆኑ እናደርጋለን?'' ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በምክር ቤቱ ቀርበው ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሃና አርእያ ስላሴ በበኩላቸው ''በህገ መንግስቱ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው መሬት የጋራ ንብረት ነው'' ብለዋል፡፡
''ይህ ሲባል አንድ ግለሰብ ኢትዮጵያዊም ቢሆን መሬትን በባለቤትነት መያዝ አይችልም፤ ይህ ሲባል የባለይዞታነት መብት ግን ሊኖረው ይችላል'' ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ስለዚህ ''የዜጎች የንብረት መብት በአጠቃላይ ህገ መንግስታዊ ጥበቃ ያለው ነው'' ያሉት ሚኒስትሯ ''ዜጎች ደግሞ መሬትን በባለይዞታነት መያዝ እንደሚችሉ ያመላክታል'' ብለዋል፡፡
የውጭ ዜጎችን በተመለከተ ግን እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ መሬትን በይዞታነት ወይም ደግሞ ቤትን በባለቤትነት መያዝን የሚከለክለው ድንጋጌ ህገ መንግስታዊ ሳይሆን በፍትሐ ብሔር ህጋችን ላይ የተቀመጠ ድንጋጌ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
''ፍትሐ ብሔር ህጉ ደግሞ አዋጅ ስለሆነ ይህንን ማስተካከል የሚቻለው ትይዩ በሆነ የህግ መአቀፍ ነው'' ያሉት ወ/ሮ ሃና ''ስለዚህም የቀረበው ረቂቅ በፍትሐ ብሔር ህጉ ላይ ከ390 እስከ 393 ድንጋጌዎች የሚስተካከል ነው'' ሲሉ መልሰዋል፡፡
ሚኒስትሯ ''ማንኛውም ሰው የውጭም ይሁን የሀገሪቱ ዜጋ የባለይዞታነት ነው እንጂ የባለቤትነት መብት ሊኖረው አይችልም የሚለው በግልጽ መቀመጥ ይኖርበታል'' ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሌላው በአዋጁ ላይ ከምክር ቤት አባላት የቀረበው ጥያቄ ረቂቅ አዋጁ የካፒታል ሽሽትን ሊያስከትል ይችላል ከኢትዮጵያዊያን ባህል፣ ወጥቶ፣ እሴትና ሃይማኖት ጋር የሚቃረኑ ባህሎች ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ በር ከፋች ነው የሚል ነው፡፡
ለጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት በፍትሕ ሚኒስቴር የህግ እና ፖሊሲ አማካሪ የሆኑት ታደሰ ካሳ(ዶ/ር) ናቸው፡፡
ታደሰ(ዶ/ር) እንደ ቀድሞ በርን ዘግቶ መቀመጥ አሁን እንደማይቻል ተናግረው ''እሴቶቻችንን የሚሸረሽሩ አሰራሮች እንዳይኖሩ ይሰራል'' ብለዋል፡፡
''የካፒታል ሽሽት እንዳይኖርም ብሔራዊ ባንክ ይህን የሚስተዳድርበት አሰራር አለው ብለዋል'' አማካሪው፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comentarios