top of page

ሰኔ 9 2017 ''ቤተሰባችን ጥለን ለስራ በወጣንበት እባካችሁ አትግደሉን'' ጉዞ የኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ጠቅላላ መሰረታዊ የሰራተኞች ማህበር

  • sheger1021fm
  • Jun 16
  • 2 min read

''ልጆቻችን፣ ቤተሰባችን ጥለን ለስራ በወጣንበት እባካችሁ አትግደሉን'' ሲል ጉዞ የኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ጠቅላላ መሰረታዊ የሰራተኞች ማህበር ተማፀነ።


የተለያየ አላማ ኖሯችሁ ''በጫካ የምትገኙ ልጆቻችን ሆነ ሌሎች አካላት እኛ ለምናስተዳድራቸው ልጅ፣ ሚስት ቤተሰብ ስንል በስራ የተሰማራን ሾፌሮች አትግደሉን ሲል የሽከርካሪዎች ማህበሩ ተናግሯል።


የጉዞ የኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ጠቅላላ መሰረታዊ የሰራተኞች ማህበር ሊቀመንበር ዮሀንስ ታምራት ''የፀጥታ መደፍረስ ያሳጣን ብዙ'' ነው ሲሉ ለሸገር ራዲዮ ነግረዋል።


''እኛ ጠብመንጃ ሳይሆን መሪ ይዘን ነው የምንዞረው'' ያሉት ሀላፊው ሾፌሮች የሚያግቱ እና ጥቃት የሚያደረሱት አካላትን ተማጥነዋል።


ከማህበራቸው አባልም በጥይት ተመትቶ ጥቃት የደረሰበት እንዳለም ሊቀመንበሩ አንስተዋል።

ree

አብዛኛው የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የሚከፈላቸው በተመላለሱት መጠን ስለሆነ፤ በተለይም መንገድ ተዘግቶ ተሽከርካሪዎች በተለያዩ ቦታዎች ለቀናት ሲቆሙ በብዙ እንደሚጎዱ አንስተዋል።


''በሀገሪቱ ጠንካራ የሆነ ለሾፌሮች መብት የሚቆምም ሆነ የሚደግፍ ማህበር የለም'' ያሉት ሀላፊው እርሳቸው የሚመሩት ማህበር ይህንን ክፍተት ለመሙላት የሚጥር መሆኑን አስረድተዋል።


በተለይ የድንበር ተሻጋሪ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ለተለያዩ አደጋዎች ተጋላጭ እንደሚሆኑና ለብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደሚዳረጉ አንስተው፤ ይህ በሚገጥማቸው ወቅትም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።


በዚህም ማህበሩ ለታመሙ፣ አደጋ ለደረሰባቸው፣ በተለያዩ ምክንያቶች ስራ ላቆሙ አባላቱ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ ዮሀንስ ነግረውናል።


ለአብነትም በሞት የተለዩ ሾፌር አባላት ቤተሰቦች፤ ችግር ውስጥ እንዳይገቡ ማህበሩ 400,000 ብር በመስጠት ይደገፋል ብለውናል።


በከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ላይ እየደረሱ ያሉ እንግልቶች መንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉም አካል ይመለከተኛል በሚል፤ መላ ሊበጅላቸው ይገባል ሲሉም አቶ ዮሀንስ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፈዴሬሽን የህዝብ ግኑኝነት ሀላፊ ወርቃለማሁ ንጋቱ በበኩላቸው፤ በየመንገዱ ለሚጠፋው የሰው ህይወት እና ለሚወድመው ንብረት ተጠያቂነቱ የአንድ ወገን አይደለም ይላሉ፡፡ አቶ ወርቃለማሁ ህገወጥ ድርጊት የሚፈፅሙትን ተጠያቂ በማድረጉ መንግስት ሀላፊነቱ ሲኖርበት ህብረተሰቡም ሊተባበር ይገባል ብለዋል፡፡

ree

የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የከባድ መኪና ሾፌሮች እየደረሱባቸው ያሉ ችግሮችን ለመቀነስ፤ ማን ምን ይስራ በሚል በአዳማ ከተማ ሰሞኑን ውይይት ተደርጓል።


በመድረኩ የተገኙት የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ ከድር ጀዋር፤ የከባድ መኪና ለሀገሪቱ የሚያበረክቱት ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ እርሳቸው በሚያስተዳድሩበት አካባቢ እነዚህ አሽከርካሪዎች በሚተላለፉበት ወቅት እንግልት እንዳይደርስባቸው በብርቱ እየሰራን ነው ብለዋል።


አሁን ላይ መጠሪያውን ''ጉዞ የኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ጠቅላላ መሰረታዊ የሰራተኞች ማህበር'' በማለት የሰየመው ማህበር ''አዳማ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች መረዳጃ እድር'' በሚል ሲሰራ የነበረ መሆኑንም ተነግሯል።


ማህበሩ ከተቋቋመ ስድስት ዓመታትን እንዳስቆጠረና፤ 450 ሾፌሮችን በአባልነት እንዳካተተም ሰምተናል።


ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…

ማንያዘዋል ጌታሁን


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page