ሰኔ 3 2017 - ሰፋ ያለ የወጣት ቁጥር ያለባት ኢትዮጵያ ወጣቶቿ ይተዳደሩበት የነበረውን የግብርና ስራ ለምን ይሆን እየጣሉ የሚወጡት?
- sheger1021fm
- 2 days ago
- 1 min read

ከገጠሩ ይልቅ ለስራ ፍለጋ በሚል ወደ ከተሞች እንዲሁም ወደ ሌሎች ሃገራት የሚፈልሱ ወጣቶች ከመሰደድ ይልቅ ባሉበት ሆነው ግብርናው ላይ እንዲሰሩ ለማድረግ የግብርና ሚኒስቴር ምን እየሰራ ይሆን? ስንል ጠይቀናል፡፡
ወጣቱ አምራች ሃይል ነው ቢባልም በኢትዮጵያ አብዛኛው በከተማም ይሁን በገጠር ያለ ወጣት መሬት የለውም፡፡
ወጣቱ ይህ ነው የሚባል የግብርና ስራ እውቀት እንደሌለውም ያደረግነው ዳሰሳ አሳይቷል የሚለው ሚኒስቴር መ/ቤቱ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት በተቀረፀው ስትራቴጂ በየዓመቱ 700 ሺህ ወጣቶች ስራ እንዲያገኙ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የነገሩን በሚኒስቴር መ/ቤቱ የማህበራዊ ጉዳይ ባለሙያ የሆኑት አቶ አብዱልጀሊል ናስር ናቸው፡፡
ወጣቶች በባህሪያቸው ሰርተው በአጭር ጊዜ ውስጥ እጃቸው የሚገባ ገንዘብ ይፈልጋሉ፤ግብርና ደግሞ ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ፣ በተለያዩ ምክንያቶች የጠበቁትን ያህል ምርት የማይገኝበት ነው፤በዚህ መሃል በመሰላቸት ትቶ መሰደድ ይመጣል ይላሉ ባለሙያው፡፡
መስሪያ ቤታቸው ግብርና እንዴት ቢሰራበት ነው ገንዘብ ሊያመጣ የሚችለው? እንዴትስ ይዘምን?በሚለው ጉዳይ ላይ እንዲሁም ሌሎች ተቋማት የወጣቶች ስብዕና ግንባታ ላይ መስራት ያለባቸውን እንዳልሰሩም ያነሳሉ፡፡
ወጣቶቹ ቀያቸውንን ትተው እንዲሰደዱ ምክንያቱ የሚሰሩበት መሬት ማጣት ቢሆንም ያላቸው የቤተሰባቸው መሬት ላይ እንዴት መስራት እንዳለባቸው አለማወቅ ነው የሚሉት ባለሙያው፤
ወጣቱ ባለበት እንዲሰራ ያገገሙ መሬቶችን ለወጣቶች እየሰጠን ነው፤ወጣቶች እየተደራጁ ለግብርና የሚውል ብድር እየተመቻቸ ነው፤በተጨማሪም የብድር አሰጣጡን ቀለል ለማድግ ያሏቸውን የቀንድ ከብቶች በማስያዝ እንዲበደሩ እየተደረገ ነው ብለውናል፡፡
በግብርናው ዘርፍ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው ወጣቶችና ሴቶች በከብት እርባታ ዘርፍ እንዲሰማሩ የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ሚኒስቴሩ ተናግሯል፡፡
ይሁንና የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ ሰዎች ጥለው የሚወጡበት ሳይሆን ተስበው የሚገቡበት እንዲሆን ለማድረግ ማዘመን እንደሚያስፈልግ እንዲሁም በተለይ የወጣቱን አስተሳሰብ ለመቀየር መስራት እንደሚያስፈልግም ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡
ምንታምር ፀጋው
Comments