ሰኔ 28 2017 - ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሰው ንግድ ለመጀመርም ከሚቸግሩ ጉዳዮች መካከል ፋይናንስና የልምድ ማነስ ነው
- sheger1021fm
- 7 hours ago
- 1 min read
ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሰው ንግድ ለመጀመርም ሆነ የፈጠራ ሀሳብ ኖሮት ወደ ስራ ለማስገባት ከሚቸግሩ ጉዳዮች መካከል ፋይናንስና የልምድ ማነስ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት አዲስ ስራ ፈጣሪዎች አቅም አንሷቸው ሲንገዳገዱ አልያም ከገበያ ሲወጡ ይታያል፡፡
ሁለቱ ጉዳዮች ከተፈታ አንድ ስራ ፈጣሪ ባለሙያ ገበያ ውስጥ እንዲቆይና ጥሩ ተወዳዳሪ መሆን ይቻላል የሚል እምነት እንዳላቸው የብሩህ ማይንድ ኮንሰልት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ደሳለኝ ነግረውናል፡፡
ብሩህ ማይንድ ኮንሰልት ለ5ተኛ ጊዜ ያዘጋጀው ልዩ ምልከታ ለኢንተርፕረነርሺፕ ኤግዚቢሽን በዘርፉ ለሚታየው የፋይናስ አቅርቦት ችግር እንዴት መቅረፍ ይቻላል? በሚለው ዙሪያ ምክክር ይደረግበታል ተብሏል፡፡
ወደ ንግዱ አለም ለሚገቡና የፈጠራ ሀሳብ ላላቸው ሰዎች ስልጠናና ማማከር አገልግሎት እንደሚሰጡ የነገሩን አቶ ሰለሞን በስራ ወቅት ወጣቶች የራሳቸውን ስራ ለመጀመር የፋይናንስ አቅርቦትና ከንግድ ጋር የተያያዙ መረጃዎች እጥረት እንደሚቸግራቸው ተገንዝቤያለሁ ብለዋል፡፡

እነዚህ ችግሮች ቢፈታላቸው ስራዎቻቸውን በሚገባ የመከወን አቅም አላቸው በማለት ያስረዳሉ፡፡
በተለይም የፋይናንስ እጥረት ወጣቶች የሚያስቡትን ስራ ወዲያው እንዳይጀምሩ ትልቁ ድርሻ የሚይዝ መሆኑን ለስራ ፈጣሪ ወጣቶች ስልጠና በምንሰጣቸው ወቅት ይነግሩናል በማለት ጠቅሰዋል፡፡
ከንግድ ስራ ማማከር ጋር በተያያዘ እንደ ሀገር ያሉን ተቋማት እጅግ ውስን ናቸው ሚሉት አቶ ሰለሞን ደሳለኝ በንግድ ስራ ላይ የሚያማክር ሁነኛና ብቁ ባለሙያ ፈልጎ ማግኘትም ችግር ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የንግድ ስራ ሲጀመር በሚገባ ተጠንቶ ሳይሆን የፋይናንስ አቅም ስላለና አንድ ግለሰብ በዛ ንግድ ላይ ውጤታማ ሲኮን ታይቶ ነው አሁን ይሄ መንገድ አይሰራም በማለት ያስረዳሉ፡፡
በዚህ ወቅት ቅድሚያ የሚያስፈልገው የገበያ ጥናትና ህብረተሰቡ ምን ይፈልጋል የሚለው ቅድሚያ ታውቆ ነው ወደ ዘርፉ መገባት ያለበት ሲሉም ነግረውናል፡፡
በዚህ ኤግዚቢሽ ለስራ ፈጣሪዎች እንዴት የፋይናንስ አቅርቦት ችግር መፍታት ይቻላል ሚለው ጉዳይ ላይ ምክክር እንደሚደረግም የሰማን ሲሆን እስከ ቅዳሜ ድረስ ይቆያል ተብሏል፡፡
በረከት አካሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments