top of page

ሰኔ 28፣ 2016 - በሱዳን ያለውን ጦርነት ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሱዳናዊያን ቁጥር 55,000 መድረሳቸው ተሰማ

  • sheger1021fm
  • Jul 5, 2024
  • 2 min read

በሱዳን ያለውን ጦርነት ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሱዳናዊያን ቁጥር 55,000 መድረሳቸው ተሰማ፡፡


በሱዳን መንግስት እና አርኤስኤፍ(RSF) በተሰኘው ፈጥኖ ደራሽ ሀይል መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከዓመት በላይ ሆኖታል፡፡


በዚህም የሀገራቸውን የእርስ በእርስ ጦርነት ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ስደተኞች እና ጥገኝነት ፈላጊዎች ቁጥር 55,000 መድረሱን የተባበሩ መንግስታ ድርጅት ከፍተኛው የስደተኞች ኮሚሽን(UNHCR) ለሸገር በላከው መግለጫ ጠቅሷል፡፡


ይህም እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ ብቻ ያለውን እንደሚያካትት አስረድቷል፡፡

ree

በጦርነቱ ምክንያት ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት መካከል ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉት ስደተኞች በሰሜን ጎንደር ዞን ከሚገኘው ‘’አውላላ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ’’ ከሁለት ወር ግድም በፊት መውጣታቸው ይታወሳል፡፡


ስደተኞቹ ከመጠለያ ጣቢያው በ1.5 ኪሎ ሜትር ርቀት በመተማ ጎንደር መንገድ ላይ እንደሚገኙም ኮሚሽኑ መናገሩ ይታወሳል፡፡


ስደተኞቹ እና ጥገኝነት ፈላጊዎቹ መጠለያ ጣቢያቸውን ለቀው የወጡት በስርቆት፣ በተደራጀ ዝርፊያ፣ ግድያ፣ ጠለፋ የመሳሰሉ ወንጀሎች ይፈፀመብናል በሚል ምክንያት እንደሆነ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡

ree

እነዚያ ከመጠለያ ጣቢያ ወጥተው በአውራ ጎዳና ላይ ውሎ እና አዳራቸውን አድርገው የነበሩ ስደተኞችን የደህንነት ስጋት ወደማይገባቸው ቦታ ለማዘዋወር መወሰኑን ኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡


በኢትዮጵያ መንግስት እና ረጂ ተቋማት ድጋፍ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ስደተኞቹን የማዘዋወር ስራ እንደሚደረግ ድርጅቱ ጠቅሷል፡፡


ይህ ግን ገንዘብ እንደሚፈልግ UNHCR ተናግሯል፡፡


በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ተመዝግበው የሚገኙ ስደተኞች እና ጥገኝነት ፈላጊዎች ቁጥር ከ1 ሚሊዮን 51,000 በላይ የደረሰ ሲሆን ከፍተኛውን ወይንም 40 በመቶውን የሚይዙት የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ናቸው፡፡


ሶማሊያዊያን በ33 በመቶ፣ ኤርትራዊያን በ17 በመቶ እንዲሁም ሱዳናዊያን 9 በመቶ በመሆን ይከተላሉ፡፡


በሀገሪቱ ውስጥ ላሉት ስደተኞች ባለንበት የፈረንጆቹ 2024 ዓመት ምግብን ጨምሮ ለሌሎች አገልግሎቶች ማሟያ 426,000,000 ዶላር ቢያስፈልገውም እስካሁን ማግኘት የቻለው ግን 23,000,000 ዶላር ወይም ከሚያስፈልገው 14 በመቶውን ብቻ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

ree

ከሚያስፈልገው ገንዘብ ቢያንስ 10,000,000 ዶላር በቶሎ ካልተገኘ በ20 የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ስደተኞች በተለይ የጤና ሁኔታ እንደሚጎዱ ድርጅቱ ስጋቱን ጠቅሷል፡፡


የገንዘቡ አለመገኘት 90,000 የሚሆኑት ስደተኛ ህፃናት ለመቀንጨር እና ለበሽታ እንደሚያጋልጣቸው ድርጅቱ ስጋት ገብቶኛል ብሏል፡፡


በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ብዛት 4.4 ሚሊዮን መድረሱን UNHCR ተናግራል፡፡


4.4 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የተመዘገቡት እስከ የካቲት ወር 2016 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ባለው ጊዜ መሆኑንን ድርጅቱ ተናግሯል፡፡


ንጋቱ ሙሉ


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page