ሰኔ 27 2017 - ''የመንገድ መሰረተ ልማቶች አካል ጉዳተኞችን አገናዝበው የሚገነቡ ባለመሆናቸው፤ ለከፍተኛ የትራፊክ አደጋ እንዲሁም የአካል ጉዳት እየዳረጋቸው ነው''
- sheger1021fm
- Jul 4
- 2 min read
በአዲስ አበባ የሚሰሩ አብዛኛዎቹ የመንገድ መሰረተ ልማቶች አካል ጉዳተኞችን አገናዝበው የሚገነቡ ባለመሆናቸው፤ ለከፍተኛ የትራፊክ አደጋ እንዲሁም የአካል ጉዳት እየዳረጋቸው ነው ተባለ፡፡
በተለይ የዚህ ጉዳት ሰለባ የሚሆኑት አብዛኛዎቹ አይነስውራን መሆናቸውንና በትራፊክ አደጋ ምክንያትም ብዙዎቹ ህይወታቸውን እያጡ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በመንገዶች ያለመመቸት በአሽከርካሪዎች ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ ሰጥቶ አለማሽከርከርና በሌሎችም ምክንያቶች ብዙ አካል ጉዳተኞች ለከፍተኛ የትራፊክ አደጋና ሞት ተዳርገዋል ተብሏል፡፡
በዚህ ምክንያት ከቤት በሰላም ወጥቶ ያሰቡት ለመድረስ በተለይ አይነስውራን ትልቅ ስጋት ሆኖባቸዋል፣ የጉዳት ሰለባም እየሆኑ ነው ሲል የኢትዮጵያ አይነስውራን ብሔራዊ ማህበር ተናግሯል፡፡
የማህበሩ የስራ አመራር ቦርድ ፕሬዝዳንት አቶ አበራ ረታ ባለፉት ሁለት ዓመታት በመንገድ ላይ በደረሰ የትራፊክ አደጋ ጉዳት የገጠማቸውና ለሞት የተደረጉ ዓይነ ስውራን በርካታ ናቸው ብለዋል፡፡
በመንገድ ላይ ያለው ሁኔታ ተደራሽ ካለመሆኑ አንፃር አንዳንድ አገራት ውስጥ ዓይነ ስውራን መንገድ በሚያቋርጡበት ሰዓት አንድም እነሱን ተመልክቶ መብራት የሚያበራ የደህንነት ካሜራ ይገጠማል ስለዚህ ካሜራው ለይቶ በራሱ በሚያበራው የትራፊክ መብራት በእንቅስቃሴ ላይ ያለ አሽከርካሪ እንዲቆም ስለሚያደርግ ከአደጋ የሚጠብቅ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ነው ይህንን ወይም ተመሳሳይ ሌሎች መላዎች በኢትዮጵያ ቢኖሩ አደጋውን መቀነስ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ማህበሩ በየጊዜው ስለችግሩ ቢያነሳም ግን ብዙ መፍትሄ አልተሰጠውምም ብለዋል፡፡
በአሽከርካሪ ጥፋት ምክንያት በቅርቡ የደረሰን የትራፊክ አደጋ የሚጠቅሱት አቶ አበራ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ሲገነቡ አካል ጉዳተኞችን አገናዝበው አለመሆኑ ለችግሩ ዋና ምክንያት ነው ይላሉ፡፡
የመረጃ ተደራሽ አለመሆን እንዲሁም የእግረኛ ማቋረጫዎችም ይሁን መጓጓዣ መንገዶች ለዓይነ ስውራን ታሳቢ ተደርገው ያልተሰሩ መሆናቸው እውነት ነው የሚሉት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ መሪ ስራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ ሲሳይ ጥላሁን በየጊዜው ለተለያዩ ተቋማት በተለይ ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከታቸው እንደ የትራፊክ ፖሊሶች፣ የመንገድ ባለሙያዎች የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ በፕሮግራሞቻቸው አካተው እንዲሰሩ እያደረግን ብለዋል፡፡
የእግረኛ ማቋረጫዎች፣ በእግረኛ መንገዶች ላይ ምሰሶዎች ወይም ጉድጓዶች መኖር የሚዳሰሱ ወይም የሚሰሙ ምልክቶች አለመኖርና ሌሎችም ምክንያቶች የአካል ጉዳተኞችን እንቅስቃሴ እንደሚገድብና ለሞት እንዲሁም ለከፍተኛ የአካል ጉዳት የሚዳርግ ነው ተብሏል፡፡
አይነ ስውራንን ጨምሮ ሌሎች አካል ጉዳተኞች በየቀኑ ሊወገዱ በሚችሉ የትራፊክ አደጋዎች ምክንያትም የሚገጥማቸው እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ የሚመለከተው ሁሉ አስፈላጊውን ትኩረት እንዲሰጠው ተጠይቋል፡፡
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il












Comments