ሰኔ 27 2017 - በአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ድግግሞሽን በቅጡ ለመቀነስ እየሰራሁ ነው ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተናገረ።
- sheger1021fm
- Jul 4
- 1 min read
የኤሌክትሪክ ሀይል መቆራረጥ ወደ ዜሮ ማስጠጋት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም መ/ቤቱ አስረድቷል፡፡
ያዘመሙ እና ያረጁ ፖሎች መኖራቸው፣ የረገቡ እና የተቀራረቡ የኤሌክትሪክ መስመሮች እና ከመሰረተ ልማቶች ጋር ተጠግተው ያሉ ዛፎች ለመቆራረጡ እንደ ምክንያት ይነሳሉ ተብሏል።
አገልግሎቱ ይህንን ያለው የኤሌክትሪክ አደጋን እና የሀይል መቆራረጥን ከመቀነስ ጋር ተያይዞ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
ለሀይል መቆራረጥ 45 በመቶውን ይይዛል የተባለው መሰረተ ልማቶቹ ከዛፎች ጋር ያላቸው ንክኪ መሆኑ የተነገረ ሲሆን ዛፎች ከኤልክትሪክ መስመር የ3 ሜትር ርቀት ሊኖራቸው ይገባል ተብሏል።
በዚህም ከመሰረተ ልማቶቹ ጋር ንክኪ ያላቸውን ከ5,000 በላይ ዛፎች ቆርጠናል ያሉት የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ አንዋር አብራር ከተያዘው እቅድም 78 በመቶ የሚሆነውን አሳክተናል ብለዋል።
በተጨማሪም ከ6,000 በላይ ያዘመሙ እና ያረጁ ፖሎችን መጠገንን እና 2400 የረገቡ መስረመሮችን ማስተካከል ላይ በትኩረት ስንሰራ ቆይተናል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ከ10,000 በላይ ትራንስፎርመሮች መኖራቸውን የተናገረው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከዚህ ውስጥ 2,000 የሚሆኑትን አቅማቸውን አሳድገናል ብሏል።
በእነዚህ እና ሌሎች ስራዎች የሀይል መቆራረጥ ችግሩን መቀነስ ቢቻልም አሁንም ግን ችግሩ በመኖሩ ስራዎቻችንን እየከወንን ነው ብለዋል አቶ አንዋር በሰጡት መግለጫ።
የሀይል መቆራረጥ ቢያጋጥም እንኳን የቆይታ ጊዜውን ማሳጠር ላይ እየሰራሁ መሆኑን ሰምተናል፡፡
በሌላ በኩል ከነገ ቅዳሜ ጀምሮ 100,000 ችግኞችን ለመትከል እቅድ መያዙን የተናገረው አገልግሎቱ ለዚህም የ20 ሚሊዮን ብር በጀት መያዙን ተናግሯል።
ፋሲካ ሙሉወርቅ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il












Comments