top of page

ሰኔ 27 2017 - መንግስት በገዳማት እና በቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ለማስቆም ለምን የፀጥታ ሃይል እንደማይመድብ ተጠየቀ፡፡

  • sheger1021fm
  • Jul 4
  • 2 min read

ይህ የተጠየቀው ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) የመንግስትን የ2017 የዕቅድ አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ለመስጠት በምክር ቤት በተሰየሙበት ወቅት ነው፡፡


የምክር ቤት አባሉ አበባው ደስአለው(ዶ/ር) በዝቋላ አቦ እና በተለያዩ ገዳማት ምንም የጦር መሳሪያ ባልታጠቁ መናኞች ላይ ሞት፣ ድብደባ እና ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑን ተናግረው፤ መንግስት ለምን በቤተክርስቲያን አገልጋዮች ላይ የሚፈጸምን ጥቃት ለማስቆም የጸጥታ ሃይል ለምን እንደማይመድብ ጠይቀዋል፡፡


መንግስት ከታጠቁ ሐይሎች ጋር ያለውን ችግር በድርድር እንዲፈታ፣ የፖለቲካ እስረኞችም እንዲፈቱ ቢጠየቅም እስረኞች በተለያዩ ክልሎች አሁንም ፍትህ አለማግኘታቸውን እንደራሴው ተናግረዋል፡፡


ree

በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉልጉሙዝ እና በመሳሰሉ ክልሎች ላይ የጸጥታ ችግሩ እካሁን አለመቀረፉን ያስረዱት አበባው ደስአለው (ዶ/ር) ሰላም እንዲመጣ አግዙን ባሉን መሰረት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ መልክተኛ ብንልክም አልተሳካልንም ብለዋል፡፡


እኛ ፖለቲከኞች ሁሉ ጊዜ ችግር መፍጠር ሳይሆን ችግሩ እንዲፈታ ቀረብ ብለን መነጋገር እንፈልጋልን ሲሉ የምክር ቤት አባሉ ተናግረው ያን መድረክ ግን ማግኘት አልቻልንም ሰላሙ እንዲመጣ ምን ይሉናል? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሰጡት ምላሽ የዝቋላ ገዳም ውስጥ አንድ አባት ተገድለዋል፣ ማን እንደገደላቸውም እየተጣራ ነው ተጣርቶም ምላሽ እንደሚገኝ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡


የሃይማኖት ተቋማት የታጠቁ ሽፍቶች መሸሸግያ ከሆኑ እንደዚህ ዓይነት አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃይማኖት ቦታ የሃይማኖት ቦታ ነው መሆን ያለበት የታጠቁ ሽፍቶች ሲሸሹ የሚደበቁበት ከሆነ ሲከፋቸው ገድለው ሊሄዱ ይችላሉ ብለዋል፡፡


12 ዓመት ተምሮ ፈተና ሊፈተን የሚሄድ ሰው ላይ የሚተኩሱ ሰዎች ዝቋላ አንድ አባት ቢገድሉ ምን ይገርማል?  ሲሉ አስረድተዋል፡፡


ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የሰላም እና የጸጥታ ችግር ዋነኛው መንስዔ የተሳሳተ የፖለቲካ ውጤት ነው ብለዋል፡፡


ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ለመገናኘትና ለመመካከር አልቻልንም ሊሚለው ምክር ቤቱ ቅሬታም እንደሚያስታውሰው ከተቃዋሚዎች ከተወያየው ወር አልሞላኝም ገና ሁለት ሳምንት ሊሞላኝ ነው ብለዋል፡፡


የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጠርቼ አወያይቻቸዋልው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእርግጥ ሽምግልና በተመለከተ የተሞከረ ነገር ካለ ጥሩ ሃሳብ ነው ፤ መቀጠል አለበት ግን ከእኔ ጋር ምንም የሚያይዘው ነገር የለም፤ አሰራሩ የታወቀ ነው ብለዋል፡፡


ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል ከሆነ ሽምግልና የሚካሄደው በክልሉ እና በሸኔ መካከል ነው የሚካሄደው እነሱን ማነጋገር ይቻላል፡፡


በአማራ ክልልም ከሆነ በክልሉ እና እዚያ ካለው ሃይል ጋር ነው የሚካሄደው እንደዛ ማድረግ ይቻላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡


ከእኔ የሚፈለግ ነገር ካለ እኔ ዝግጁ ነኝ ያሉት አብይ አህመድ (ዶ/ር) በቀጥታ ከኔ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ  ግን አይደለም ብለዋል፡፡


እዛ ያሉ የታጠቁ ሃይሎች ከወረዳቸው፣ ከዞናቸው እና ከክልላቸው ጋር ተደራድረው መግባት ይችላሉ፤ እየገቡም ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡


ያሬድ እንዳሻው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page