ሰኔ 20 2017 - የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር፤ በሪፖርቱ ላይ የታዓማኒነት ጥያቄ ከፓርላማው ቀረበበት፡፡
- sheger1021fm
- Jun 27
- 2 min read
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ባለፉት 11 ወራት 960 ሚሊዮን ህዝብ ማጓጓዙን ቢናገርም፤ በሪፖርቱ ላይ የታዓማኒነት ጥያቄ ከፓርላማው ቀረበበት፡፡
ሚኒስትሩ በበኩላቸው ‹‹ከአቅም በላይ በሆኑ ቦታዎች ላይ ነው የትራንስፖርት አገልግሎት የተቋረጠው እንጂ በሌሎች አካባቢዎች ዋጋ እየተከፈለም ቢሆንም የትራንስፖርት እንቅስቃሴ አለ›› ብለዋል፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሪፖርት ላይ የታዓማኒነት ጥያቄ የተነሳበት መስሪያቱ የ11 ወር የስራ ክንውን ሪፖርቱን ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡
ሪፖርቱን በንባባ ያቀረቡት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ 913 ሚሊዮን ሕዝብ ለማጓጓዝ ታቅዶ 96ዐ ሚሊዮን ህዝብ በማጓጓዝ ከዕቅድ በላይ ፈፅመናል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ የአንድ አገር አቋራጭ አውቶብስ አማካይ ዓመታዊ ኪሎ ሜትር ሽፋን በዓመቱ 1ዐ7,000 ኪሎ ሜትር ለማድረስ ታቅዶ 1ዐ5,000 ኪሎ ሜትር በማድረስ ውጤታማ ስራ ከውነናል ሲሉ በምክር ቤት ቆይታው ተናግረዋል፡፡
የሪፖርቱን ማብቃት ተከትሎ ጥያቄ የጠየቀው የከተማ፣መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጸጥታ እና በተለያዩ ምክንያቶች የመንገድ ትራንስፖርት ከሁለት ዓመት በላይ በተቋረጠባቸው አካባቢዎች የሚኖረው የህብረተሰብ ክፍል ከኑሮ ውድነቱ በተጨማሪ ለህክምና እና ለተለያዩ አስገዳጅ ማህበራዊ ጉዳዮች ለሚደርገው ጉዞ ከአቅሙ ባለይ እየከፈለ በአየር ትራንስፖርት እየተጓጓዘ መሆኑ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ሚኒስቴሩ ግን በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በድግግሞሽ 960 ሚሊዮን ህዝብ ማጓጓዙን ተናግሯል ያለው ቋሚ ኮሚቴ ለመሆኑ ይህ አፈጻጸም መሬት ላይ ካለው ነባራዊ ሃቅ ጋር ምን ያክል ተጨባጭ ነው? ሲል ጠይቋል፡፡
የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎት በተቋረጠባቸው አካባቢዎችስ ዳግም አገልግሎቱን ለማስጀመር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምን እየሰራ ነው ሲል ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡
ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር እንዳለ ሁላችንም እናውቃለን ብለዋል፡፡
ትራንስፖርት የተቋረጠው በተወሰኑት እና ከአቅም በላይ በሆኑ ቦታዎች ላይ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ከዚያ ውጭ ዋጋ እየተከፈለበትም ቢሆን የትራንስፖርት አገልግሎት አለ ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በአስቸጋሪ መልካ ምድር፣ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሁሉ ውስጥ ተጓዡም አሽከርካሪውም ይንቀሳቀሳል ያሉት አለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንቅስቃሴ ስላለ ነው አጓጉዘናል ያልነው ህዝብ ቁጥር ምንም የሚያጠራጥር አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ የተሻለ ምቹ ሁኔታ ቢኖር ደግሞ ከዚህ በላይ ይንቀሳቀሳል ብለዋል ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶ/ር)፡፡
የጸጥታ ሁኔታ በተሻሻለበት አካባቢዎች ትራንስፖርቱን የማስጀመር ስራ እየተሰራ እንደሆነ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il








