ሰኔ 13 2017 - ለሴቶች የተለየ የባንክ አገልግሎት በማቅረብ ምስጉን ስራ በመስራት ቀዳሚ ባንክ መባሉን እናት ባንክ ተናገረ
- sheger1021fm
- 10 hours ago
- 1 min read
ለሴቶች የተለየ የባንክ አገልግሎት በማቅረብ ምስጉን ስራ በመስራት ቀዳሚ ባንክ መባሉን እናት ባንክ ተናገረ።
አብዛኞቹ ሀላፊዎች ሴት መሆናቸው እንዲሁም በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ያለ ዋስትና መስጠት መቻሉ እናት ባንክን ቀዳሚ ባንክ ያስባለው ሌላው ምክንያት ተደርጎ ተጠቅሷል።
እናት ባንክ ቀዳሚ ባንክ የተባለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዓለም ባንክ የሥርዓተ-ፆታ ፈጠራ ጋር በመተባበር ባካሄዱት የ2025 የባንኮች የስርዓተ ፆታ አካታችነት ምዘና መስፈርት መሰረት መሆኑ ተጠቅሷል።
በዚህም እናት ባንክ የተሻለ ስራ በመስራቱ ከ30 የኢትዮጵያ ባንኮች የመጀመሪያና ብቸኛ ባንክ ሆኗል ሲባል ሰምተናል።

ለሴቶች የተለየ የባንክ አገልግሎት ማቅረብ፣ በፈጠራ የተደገፈ የባንክ አሠራር መዘርጋት እንዲሁም ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንኮች ሁሉን አካታችነት የባንክ አገለግሎት መስፈርቶች መሆናቸው ተነግሯል።
እናት ባንክም እነዚህን መስፈርቶች በሟሟላቱ ቀዳሚ ባንክ መባል ችሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ከባንኩ ከ55 በመቶ በላይ አመራሮች ሴቶች መሆናቸው፣ ከ22,000 በላይ ለሆኑ ስራ ፈጣሪ ሴቶች 1.4 ቢሊየን ብር ካለ ዋስትና በማበደር የራሳቸውን ስራ እንዲጀምሩ መደረጉ ተነስቷል።
እንዲሁም ሴቶች ላይ ብቻ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራ ክፍል በማዋቀር ሴቶችን በቢዝነስና መሰል ስራዎች የማማከር ስራ እየሰራ በመሆኑ ከተመረጠባቸው መስፈርቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
ይህ የብሄራዊ ባንክ እና የአለም ባንክ የአካታችነት የምዘና መስፈርት የፋይናንስ ተቋማት ሴቶችን እንደ ደንበኛ፣ ሠራተኛ እና አመራርነት ያላቸውን አካታችነት ለመገምገም የሚረዳ ሲሆን በዘርፉ አመራር ላይ ያለውን ልዩነት ለማጥበብም የሚያግዝ ነው ተብሎለታል።
ንጋቱ ሙሉ
Comments