ሰኔ 11 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች
- sheger1021fm
- Jun 18
- 2 min read
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራኑ የበላይ መሪ አያቶላህ ዓሊ ሐሚኒ የት እንደተደበቀ አሳምረን እናውቃለን አሉ፡፡
ልንገድለው ብንችልም ያን ማድረግ አንመርጥም ብለዋል ትራምፕ፡፡
የኛ ፍላጎት ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ እጅ እንዲሰጥ ነው ማለታቸው አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡
የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ ዓሊ ሐሚኒ ለፅዮናዊያን አንዳች ምህረት እንደሌለን እናሳያቸዋለን ሲሉ መዛታቸው ተሰምቷል፡፡
ከእስራኤል ጋርም ጭራሽ አንደራደርም ብለዋል ሐሚኒ፡፡
ባለፉት 5 ቀናት ግጭቱ የእስራኤል እና የኢራን ተደርጎ ሲቆጠር ሰንብቷል፡፡
ከእስራኤል ጦር በተጓዳኝ ትራምፕም ትናንት የኢራኗ ርዕሰ ከተማ ቴሕራን ነዋሪዎች በሙሉ ለቅቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቃቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡
ቴህራን የ10 ሚሊዮን ገደማ ኢራናውያን መሆኗ ይነገራል፡፡
ብዙዎቹ የቴሕራን ከተማ ነዋሪዎች በዚህ ቅጽበት እንዴት እና ወዴት እንሂድ በሚል ግራ ተጋብተዋል፡፡
ከተማዋን ለቅቀው የሚወጡም ብዙዎች እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ የሀገራቸው ጦር የእስራኤልን የኢራን ድብደባ እንዲያግዝ ፍላጎት አላቸውም ተብሏል፡፡
በዚሁ ጉዳይ ፕሬዘዳንቱ በብርቱ እያሰቡበት ነው መባሉን CBS ፅፏል፡፡
ይሁንና ከፀጥታ እና ደህንነት አማካሪዎቻቸው ጋር ቁርጥ ካለው ውሳኔ ላይ አልደረሱም ተብሏል፡፡
እስራኤል በተለይም ከተራሮች ስር በ90 ሜትር ጥልቀት ተገንብቷል የሚባለውን የፎርዶ የዩራኒየም ማብለያ ተቋምን ለማደባየት የአሜሪካ እርዳታ እንደሚያሻት ይነገራል፡፡
እስራኤል ደግሞ ይሄን መሰሉ ዋሻ ሰርሳሪ ቦምብ የላትም፡፡
ይሄን ተቋም ለመምታት የአሜሪካንን ድጋፍ እየጠበቀች መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
የእስራኤል እና የኢራን መጠቃቃት ተባብሶ መቀጠሉን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
አብዮታዊ ዘብ የተሰኘው የኢራን የጦር ክፍል በእስራኤል ላይ ዘመን አፈራሹን የፋታህ 1 ሚሳየል መተኮስ ጀምሬያለሁ ብሏል፡፡
ሚሳየሉ ለማንኛውም የሚሳየል መከላከያ ጋሻ የማይበገር ነው ተብሏል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ከእስራኤል ጦር በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡
እስራኤል በኢራን ላይ በቀጠለችው ድብደባ በርዕሰ ከተማዋ ቴሕራን ምስራቃዊ ክፍል የከባድ ከባድ ፋንዳታ መሰማቱን በመረጃው ተጠቅሷል፡፡

እስራኤል እና ኢራን በከባዱ እየተበቃቀሉ ነው፡፡
የእስራኤል ጦር ሌሊቱን በኢራኗ ርዕሰ ከተማ ቴህራን እና ሌሎችም ቦታዎች የሚገኙ የመሳሪያ ማምረቻዎችን አደባይቻለሁ ማለቱን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
ኢራንም በሌሊት ድብደባዋ በእስራኤል የአየር ሀይል ሰፈር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት አድርሻለሁ ማለቷ ተጠቅሷል፡፡
ከኢራን የተተኮሰ ሚሳየል በማዕከላዊ እስራኤል ከባድ ቃጠሎ መቀስቀሱ ተሰምቷል፡፡
ወደ እስራኤል ሜሮን የአየር ሀይል ሰፈር የተተኮሰው የኢራን ሚሳየል ዒላማውን ስለመምታቱ ከገለልተኛ ወገን የተገኘ መረጃ የለም ተብሏል፡፡
እስራኤል በኢራን ላይ የፈፀመችው ድብደባ ኢራን በእስራኤል ላይ ካደረሰችው በ5 እጥፍ የላቀ መሆኑን የጦር ጉዳይ ተከታታዮች ተናግረዋል፡፡
እስራኤል በኢራን በተያያዘችው ድብደባ አውሮፓውያኑ የአቋም መከፋፈል እያሳዩ ነው፡፡
ፈረንሳይ በዚህ ድብደባ በኢራን የሥርዓት ለውጥ ማስከተል የሚለውን ሀሳብ በብርቱ ተቃውማለች፡፡
ጀርመን በፊናዋ እስራኤልን የእኛን ስራ ስለሰራሽልን እናመሰግናለን ማለቷን የፃፈው ደግሞ ቢቢሲ ነው፡፡
የኢራን ጦርም የእስራኤሏ ኔብ ዜዴክ ከተማ ነዋሪዎች ለቅቀው እንዲወጡ በብርቱ አስጠነቀቃቸው፡፡
ኔቭ ዜዴክ በቴል አቪቭ አቅራቢያ የምትገኝ ከተማ እንደሆነች አናዶሉ ፅፏል፡፡
የኢራን ጦር የኔቭ ዜዴክ ከተማ ነዋሪዎች ለራሳቸው ደህንነት ሲሉ በአጣዳፊ ለቅቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቁ ተሰምቷል፡፡
ቀደም ሲል የእስራኤል ጦር ተከትሎም የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራኗ ርዕሰ ከተማ ቴሕራን ነዋሪዎች ለቅቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቃቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡
እስራኤል በኢራን በፈፀመችው ድብደባ የተገደሉ ሰዎች ብዛት 585 ደርሷል፡፡
ከሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ አካላዊ ጉዳት ገጥሟቸዋል፡፡
ኢራን በእስራኤል ላይ በፈፀመው ጥቃት 24 ሰዎች መገደላቸው ተጠቅሷል፡፡
የብራዚል የቀድሞ ፕሬዘዳንት ጂየር ቦልሶናሮ መንግስታዊ አውታርን ተጠቅመው የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ሲያሰልሏቸው ነበር ተብለው ተወነጀሉ፡፡
ጋዜጠኞች እና የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾችን የበልሶናሮ ህገ-ወጥ የስለላ ተግባር ሰለባዎች እንደነበሩ ለፍርድ ቤት የቀረበ ማስረጃ ማሳየቱን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
ቦልሶናሮ በፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸው ላይ ስለላ ሲያስፈፅሙ ነበር የተባለው በምህፃሩ አቢን በተሰኘው መንግስታዊ የደህንነት ተቋም አማካይነት ነበር ተብሏል፡፡
አቢን የቦልሶናሮን የፖለቲካ ተቀናቃኞች እና የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾችን ለመሰለል እስራኤል ስሪት ሶፍትዌር ሲጠቀም እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
ቦልሶናሮ የልጃቸውን ከግብር ጋር የተያያዘ ጉዳይ ሲመረምሩ የነበሩ ባለሙያዎችንም በሚስጥር ያሰልሉ እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡
የቀድሞው የብራዚል ፕሬዘዳንት በምርጫ ከተሸነፉ በኋላ በመንግስት ግልበጣ ስልጣን ላይ ለመቆየት ባደረጉት ሙከራ ተከስሰው ፍርድ ቤት እየተመላለሱ ነው ተብሏል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments