top of page

ሰኔ 11 2017 - በትግራይ አጀንዳ ማሰባሰብ እንዴት ይከወን በሚለው ጉዳይ ከክልሉ ጊዜዊ አስተዳደር ጋር ተደጋጋሚ ውይይት እያደረገ መሆኑን የምክክር ኮሚሽን ተናግሯል

  • sheger1021fm
  • 8 hours ago
  • 2 min read

በትግራይ ክልል ለሃገራዊ ምክክሩ አጀንዳ ለማሰባሰብ ስራዎች ተጀምረዋል፡፡


በክልሉ አጀንዳ ማሰባሰብ እንዴት ይከወን በሚለው ጉዳይ ዙሪያ ከክልሉ ጊዜዊ አስተዳደር ጋር ተደጋጋሚ ውይይት እያደረገ መሆኑን የብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን ተናግሯል፡፡


ከትግራይ ክልል በስተቀር በአዲስ አበባንና ድሬደዋ ከተማ አስተዳድሮች እንዲሁም በሁሉም ክልሎች ሊመከርባቸው ይገባል የተባሉ አጀንዳዎችን ሲያሰባስብ የቆየው ኮሚሽኑ ወደ ትግራይ ክልል ገብቶ አጀንዳዎችን ለማሰባሰብ የሚያስችሉትን ውይይቶች እያደረገ መሆኑን ነግሮናል፡፡


በክልሉ አሁን በስራ ካለው ጊዜያዊ አስተዳደር፣ በክልሉ ካሉት 4ቱም ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከምሁራን፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በየደረጃው እየተደረጉ ባሉ ውይይቶች ስራው እንዴት ይሰራ በሚለው ጉዳይ ዙሪያ እየተነጋገሩ መሆኑን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) ነግረውናል፡፡

ለመሆኑ አሁን ባለው ሁኔታ የተባለውን አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ ለመከወን ይቻላል ወይ? ስንል የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹን አቶ ምዑዝ ገብረ ሂወትን ጠይቀናቸዋል፡፡


እርሳቸው እንደሚሉት አሁን በትግራይ ክልል ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ ሰላም አለ፤ አጀንዳ ማሰባሰብ እንቅፋት የሚሆን ምንም ነገር የለም ብለዋል፡፡


በሰላምና በእርቅ ጉዳይ ላይ በግላቸው እየሰሩ መሆኑን የነገሩን አቶ ምዑዝ ወደ ትግራይ ክልል ከመግባቱ በፊት ሃገራዊ ምክክሩ ለትግራይ ህዝብ ምን ይዞለት ይመጣል? ጠቀሜታውስ ምንድነው የሚለውን ለህዝቡ ማስረዳት ይጠበቅበታል፤ ኮሚሽኑ ዝግጁ ከሆነ እኛም እንደ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት እናግዘዋለን ብለዋል፡፡


ግጭት፣ ጦርነት፣ ሰላም ማጣት በብዙ ፈትኖናል እንድንራራቅም ምክንያት ሆኗል የሚሉት የሰብኣዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ምኡዝ ገብረሂወት፣ ከዚህ በኋላ በተቻለ መጠን ከኮሚሽኑ ጋር ሆነን የጋራ መፍትሄ ማፈላለግ ይኖርብናል ሲሉም አስረድተዋል፡፡


ይሁንና እኛ በዚህ ደረጃ ፍላጎቱ ቢኖረንም ኮሚሽኑ አላቀረበንም ሲሉም ቅሬታቸውን ተናግረዋል፡፡


ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል የሚሰራውን ስራ ለማገዝ ዝግጁ የሆኑ ከፖለቲካም ገለልተኛ የሆኑ ከ500 በላይ ሰዎችን ወደ ትግራይ ክልል ለመላክ እንደተዘጋጁም ጠቅሰዋል፡፡


ባሳለፍነው ወር ከግንቦት 22 እስከ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ተካሂዶ በነበረው የፌዴራል ተቋማትና ማህበራት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ማጠናቀቂያ ላይ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እስከ ሃምሌ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የትግራይ ክልልን አጀንዳ ለማሰባሰብ ውጥን መያዛቸውን መናገራቸው ይታወሳል፡፡


ምንታምር ፀጋው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page