top of page

ወጋገን ባንክ 10 ሚሊዮን ዶላር የሚስገኝለትን ስምምነት የዓለም ባንክ አባል ከሆነው የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ጋር ተፈራረመ፡፡

  • Apr 14
  • 2 min read

ሚያዝያ 6/2018


ወጋገን ባንክ 10 ሚሊዮን ዶላር የሚስገኝለትን ስምምነት የዓለም ባንክ አባል ከሆነው የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) ጋር ተፈራረመ፡፡


አላማውም የንግድ ፋይናንስ ዋስትና ለመስጠት ነው ተብሏል፡፡


ስምምነቱን የወጋገን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ውበት እና የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ፣ ማላዊ እና ዛምብያ የካንትሪ ማኔጀር የሆኑት ማዳሎ ሚኖፉ ፈርመውታል፡፡


ስምምነቱ ለወጋገን ባንክ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን አስር ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያስገኝለት ሲሆን ይህም ባንኩ በወጪና ገቢ ንግድ ዘርፍ ለተሰማሩ ደንበኞቹ የበለጠ ተደራሽ እና ቀልጣፋ የፋይናንስ ዋስትና አገልግሎት መስጠት ያስችለዋል ተብሎ ታምኖበታል፡፡



ስምምነቱ የንግድ ዋስትና በመስጠት በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮችን ንግድ ለማጎልበት እና በንግድ ስርዓቱ ላይ የሚያጋጥማቸውን ስጋቶችን ለመቀነስ ያለመ ሲሆን ወጋገን ባንክም በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን በተዘረጋው የግሎባል የንግድ ፋይናንስ ፕሮግራም ተጠቃሚ ለመሆን ያስችለዋል ተብሏል፡፡


የወጋገን ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አክሊሉ ውበት ስምምነቱ ባንኩ በገቢ እና ወጪ ንግድ ለተሰማሩ ደንበኞቹ የሚሰጠውን አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ ከማሳደግ አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡


ዋና ሥራ አስፈፃሚው አክለውም ወጋገን ባንክ ከአይ ኤፍ ሲ ጋር ያለውን አጋርነት ወደ ሌሎች ዘርፎች በማሳደግ አካታች የፋይናንስ አገልግሎት ለማቅረብ እና ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት እያበረከተ ያለውን አስተዋፅዖ ለማጎልበት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።


የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ካንትሪ ማኔጀር የሆኑት ማዳሎ ሚኖፉ በበኩላቸው በርካታ የንግድ ድርጅቶች በተለይም አነስተኛ እና መካከለኛ ድርጅቶች በወጪ እና ገቢ ንግዳቸው ላይ የፋይናንስ ውስንነት እያጋጠማቸው በሚገኙበት ወቅት ሰምምነቱ መደረጉ ድርጅቶቹ አስፈላጊ ግብዓቶችን በጊዜ እንዲያገኙ፣ የገበያ ፍላጎትን እንዲያሟሉ እና ከዓለምአቀፍ ገበያ ጋር በይበልጥ እንዲገናኙ ያግዛቸዋል ብለዋል፡፡


ከንግድ ፋይናንስ ዋስትና በተጨማሪ ስምምነቱ የባንኩን የአደጋ አስተዳደር እና የትሬዠሪ ተግባራት ለማጠናከር የማማከር አገልግሎትን የሚያካትት ሲሆን የባንኩን አሰራር በማጎልበት ሥራ ፈጠራን እና የግል የዘርፍ እድገትን በይበልጥ ለመደገፍ ጠንካራ አቅም እንደሚፈጥም አስረድተዋል፡፡


ከዚህ ቀደም ወጋገን ባንክ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ጋር በትሬዠሪ ማኔጅመንት፣ የወጪና ገቢ ንግድ እንዲሁም የስጋት ቁጥጥር እና አስተዳደር ዙሪያ የምክር አገልግሎት ማግኘት የሚያስችለውን ስምምነት መፈራረሙን ከላከልን መግለጫ ላይ ተመልክተናል፡፡


ንጋቱ ሙሉ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


YouTube : https://shorturl.at/18TS1

WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx

X :- https://x.com/shegerfm?s=2

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page