ሚያዝያ 30 2017 - በሸገር ከተማ አስተዳደር ከዚህ በኋላ ደንብ ተላላፊ አሽከርካሪዎችን ለመቅጣት መንጃ ፍቃድ መቀበል፣ የመኪኖችንም ታርጋ መፍታት አይኖርም ተባለ።
- sheger1021fm
- 3 hours ago
- 1 min read
በሸገር ከተማ አስተዳደር ከዚህ በኋላ ደንብ ተላላፊ አሽከርካሪዎችን ለመቅጣት መንጃ ፍቃድ መቀበል፣ የመኪኖችንም ታርጋ መፍታት አይኖርም ተባለ።
አሽከርካሪዎች ጥፋት ከፈጸሙበት ቦታ ሳይንቀሳቀሱ ቅጣታቸውን መክፈል የሚችሉበት አዲስ ቴክኖሎጂ ስራ ላይ ማዋሉን የከተማ አስተዳደሩ ይፋ አድርጓል።
ስራ ላይ የዋለው አዲሱ ቴክኖሎጂ ሞያተኞች ከአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመሆን ያበለፀጉት እንደሆነ ሠምተናል።

ረጅም ጊዜ ከፈጀ ሙከራ እና ፍተሻ በኋላ ባለፈው ቅዳሜ ስራ ላይ መዋል መጀመሩን የሸገር ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ያሲን አህመድ ነግረውናል።
ቴሌብር ያላቸው አሽከርካሪዎች ይህንኑ በመጠቀም ፤ የሌላቸው ደግሞ ለዚሁ የተዘጋጀውን መተግበሪያ በማውረድና፤ ከባንክ ሂሳባቸው ገንዘብ ተቀናሽ በማድረግ ቅጣታቸውን መክፈል የሚችሉበት ቴክኖሎጂ ነው ብለዋል።
ከዚህ በኋላ በከተማ አስተዳደሩ ሲንቀሳቀሱ ደንብ የተላለፉ አሽከርካሪዎች ቅጣት እስኪከፍሉ በሚል የመንጃ ፍቃዳቸው እንደማይወሰድ እና የመኪናቸው ታርጋም እንደማይፈታ ተነግሯል።
/ለቅጣት የሚከፈለውን ብር መጠንም ቴክኖሎጂው በራሱ ያሳውቃል ተብሏል።
ቴክኖሎጂው በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ጭምር ፍተሻ ተደርጎበት ውጤታማነቱ የተረጋገጠ ነው የሚሉት አቶ ያሲን ለዚህም የምስክር ወረቀት እንደሰጠ አክለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ደግሞ የትራንስፖርት እና የትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን አሰልጥኖ ወደ ስራ አስገብቷል ብለዋል።
ቴክኖሎጂው ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ይባከን የነበረውን ጊዜ እና ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ የሚያስቀር እንደሆነ አቶ ያሲን ተናግረዋል።
የአሽከርካሪዎች እንግልትም ከዚህ በኋላ አይኖርም ብለዋል።
መንግስት የቅጣት ደረሰኞችን ለማተም እስከ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር ያወጣ እንደነበር ያስታወሱት ሃላፊው ይህም ገንዘብ በዚህ ቴክኖሎጂ ይድናል ብለዋል።
ቴክኖሎጂው በሙከራ ደረጃ እያለ 2146 ደንብ ተላላፊ አሽከርካሪዎች ቅጣታቸውን ከፍለውበታል ተብሏል።
የተቀጡት አጠቃላይ ገንዘብ 2.7 ሚሊየን ብር እንደሆነ አቶ ያሲን ነግረውናል።
ንጋቱ ረጋሳ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://shorturl.at/21bFN