ሚያዝያ 29 2017 - የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርን አስመልክቶ ባለፉት ዓመታት የተሰሩ ስራዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተመከረባቸው ነው
- sheger1021fm
- 2 hours ago
- 1 min read
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርን አስመልክቶ ባለፉት ዓመታት የተሰሩ ስራዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተመከረባቸው ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና ሰላም ሚኒስቴር ባዘጋጁት ውይይት ላይ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዮናስ አዳዬ ምክክር የሚያስፈልገው መንግስት ወይም አገር የእልውና ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ሲገባ ነው ብለዋል፡፡
አገር በቀል እውቀትን መሰረት ያደረገ እና ለሰው የማይቻል ሁሉ ለፈጣሪ ይቻለዋል የሚል በተጀመረው አገራዊ ምክክር ላይ ከ120 ሺህ በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል ሲሉ ዶ/ር ዮናስ ተደምጠዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የወጣቶች ህብረት እንዲሁም የሴቶች ማህበራትን ጨምሮ በርካታ ባለድርሻዎች ባለፉት አመታት በውይይቱ ላይ ተሳትፎ አድርገዋል ፣ አጀንዳዎቻቸውንም አቅርበዋል ሲሉ ዶ/ር ዮናስ ተናግረዋል፡፡
በመጪዎቹ ሁለት እና ሶስት ሳምንታት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሃይማኖት ተቋማት መከላከያ እንዲሁም ከተለያዩ የአገሪቱ ተቋማት ከተወከሉ ወኪሎች ጋር ውይይት በማድረግ አጀንዳ ያሰባስባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዶ/ር ዮናስ ተናግረዋል፡፡
ባለፉት 3 አመታት ነበሩ ከተባሉ ችግሮች መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የቀረበው ከአስራ ሶስት የማያንሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ከሂደቱ ውጪ መሆን አሳሳቢ በመሆኑ አጀንዳዎቻቸው እና ጥያቄዎቻቸው እንዲሁም ስጋታቸው በመንግስት ጆሮ እንዲያገኝ ምክር ቤቱ እየሰራ ነው ሲሉ የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር አብዱልቃድር ተናግረዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪም ፓርቲዎቹ ሀሳቦቻቸውን ሰብሰብ አድርገው በዶክመንት ደረጃ እንዲያቀርቡ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የአገራዊ ምክክር ስራው የፖለቲካ ምክክር ነው የሚል እምነት እንዳለው የአገራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተናግሯል፡፡
የሀሳብ ፣ የቃላት እንዲሁም በመሬት ላይ ያሉት ግጭቶችና ችግሮች የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዋና ዋና ችግሮች እንደነበሩ ዶ/ር ዮናስ ሲናገሩ ሰምተናል፡፡
የዛሬው ውይይት ቀጣይ በኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በኩል የሚደረጉ አስተዋፆችና በኮሚሽኑ በኩል የሚሰሩ ቀጣይ ስራዎች የሚታወቁበት ነው ተብሏል፡፡
የኔነህ ሲሳይ