ሚያዝያ 28 2017 - ኢትዮጵያ በአሜሪካ የ10 በመቶ ቀረጥ ብቻ እንድትከፍል መሆኗ የውጭ ባለበሀብቶችን እንድትስብ መንገድ ከፍቷል'' የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን
- sheger1021fm
- 3 hours ago
- 1 min read
ኢትዮጵያ በአሜሪካ አነስተኛ የተባለው የ10 በመቶ ቀረጥ ብቻ እንድትከፍል ከተወሰነባቸው ሃገራት መካከል መሆኗ የውጭ ባለበሀብቶችን እንድትስብ መንገድ ከፍቷል ሲል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ተናገረ፡፡
ከሰሞኑ እንኳን ከጃፓን፣ ከቬትናም፣ ከቻይና እና ከህንድ የመጡ ባለሃብቶች በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖቹ ገብተው ለመስራት የቅድመ ኢንቨስትመንት ምልከታ ማድረጋቸው ተጠቅሳል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ አሜሪካ ምርቶቻቸውን በሚልኩ 100 ሀገራት ላይ ታሪፍ መጣላቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ ላይ የተጣለው ታሪፍ 10 በመቶ ሲሆን በሁሉም ሀገራት ላይ የጣሉት የመነሻ ታሪፍ ወይም #Baseline_Tariff እንደሆነ ተመልክቷል።
ታሪፉ በአሜሪካ የሚገኙ ገዥዎች ለኢትዮጵያ ምርቶች ያላቸው ፍላጎት እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል በማለት የምጣኔ ሃብት ባለሞያዎች መናገራቸው ይታወሳል።

በዚያው አንጻር አስር በመቶ መሆኑ ለኢትዮጵያ በጎ ጎን ሊኖረው ይችላልም ብለዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንም ትራምፕ በሌሎች ሀገራት የጣሉት ከፍተኛ ታሪፍ፤ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በሚገኙ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ገብተው ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት እየጨመረው ነው ብለዋል፡፡
በኮርፖሬሽኑ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን እና ማርኬቲንግ ዘርፍ ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘመን ጁነዲ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ካላት ምቹ የተፈጥሮ ሃብት ፤ አቅም ያለው ወጣት እና ከምትሰጣቸው ማበረታቻዎች ጋር ተደማምሮ የባለሃብቶች ምርጫ እየሆነች ነው።
በኢትዮጵያ ከሚገኙ አስራ ሶስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች አስሩ ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን እንዲያድጉ መወሰኑ ይታወሳል።
በዚህም ቀደም ሲል ከሚታወቁበት የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ምርት ተሽከርካሪዎችን ወደ መገጣጠም እና የግብርና ምርቶችን ወደ ማቀነባበር ማደጋቸው ተጠቅሷል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ እያደገ ነው በሚባለው የሶላር ሃይል ዘርፍም ባለሃብቶች ገብተው እየሰሩባቸው እንደሚገኙ አቶ ዘመን ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም ቶዮ ሶላር የሚባለው እና የቬትናም ፤ የጃፓን እና የቻይና መሰረት ያለው ግዙፍ ኩባንያ ከአንድ መቶ ሚሊየን ዶላር በላይ ኢንቨስት በማድረግ በሃዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ኩባንያው የመጀመሪያ ምርቱን ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ መካከለኛው ምስራቅ፤ ህንድና አሜሪካ መላኩን ነግረውናል፡፡
ንጋቱ ረጋሳ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
Comments