ሚያዝያ 28 2017 - ህገ ወጥ የማዕድን ቁፋሮ እና ዝውውር ውስጥ የክልሎች እና የአካባቢው ባለስልጣናት እጅ እንዳለበት የምክር ቤት አባል ተናገሩ
- sheger1021fm
- May 6
- 1 min read
ህገ ወጥ የማዕድን ቁፋሮ እና ዝውውር ውስጥ የክልሎች እና የአካባቢው ባለስልጣናት እጅ እንዳለበት የምክር ቤት አባል ተናገሩ፡፡
የምክር ቤት አባሉ አቶ ብርሃኑ ጎበና ይህን የተናገሩት የገቢዎች ሚኒስቴር የዘጠኝ ወር የስራ ክንውን ሪፖርቱን ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡
የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ማዕድናቱ ወደ ሚገኙባቸው ክልሎች እና አካባቢዎች ለመስክ ምልከታ በሄዱበት ወቅት በአካባቢው የተሰማሩ የጸጥታ ሃይሎች፤ ህገ ወጥ የማዕድን ቁፋሮ፣ ዝውውር እና ሽያጭ በክልሉ እንዲሁም በአካባቢው ባለስልጣናት ጭምር እንደሚካሄድ ነግረዋቸዋል ብለዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባል አቶ ብርሃኑ ጎበና በጸጥታ ሃይሎች የሚያዙ ህገ ወጦች ከክልል እና ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር የጥቅም ትስስር እና የስጋ ዝምድና ያላቸው በመሆኑ ህገ-ወጦች ሲያዙም በአመራሮች እንዲፈቱ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ህግ ወጦቹ በአመራር ትእዛዝ ከተፈቱ በኋላም ለህግ እንደማይቀርቡ የምክር ቤት አባሉ አክለዋል፡፡
ይህንንም የጸጥታ አካላት በምሬት ይናገራሉ ያሉት አቶ ብርሃኑ ይህን ችግር ለመፍታት ምን እየተሰራ ነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ገቢዎች ሚኒስቴር በበኩሉ በዚህ ደርጊት ውስጥ ያሉ ባለስልጣናት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስቧል፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር የ9 ወራት የስራ ክንውን ሪፖርትን ያቀረቡት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ በለውጡ ምክንያት የማዕድን መስክ በተለይ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ከማስገኘት አኳያ ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
ይሁንና ማዕድን አሁን በህገ ወጥ መንገድ ገበያ ላይ ይውላል፤ ይመረታልም ያሉ ሲሆን በዚህ ሂደት ውስጥ ያሉ ባለስልጣናት ከዚህ ድርጊታቸው ተቆጥበው ለህዝብ አገልግሎት የሚውልበት ላይ መስራት አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ችግሩ እልባት እንዲያገኝ ጉዳዩ ከሚያገባቸው ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ ጉዳዩ የማህበረሰቡንም ድጋፍ የሚሻ ነው ብለዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
Comentarios