ሚያዝያ 24 2017 - የህግ አወጣጥ ሳይንስና በተግባር ያለው ልምድ ምን ያሳየናል?
- sheger1021fm
- 10 hours ago
- 2 min read
በየጊዜው አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ይመለከታቸዋል በሚባሉ አካላት ይወጣሉ፤ በፓርላማው እንዲሁም በየደረጃው ባሉ ምክር ቤቶች ፀድቀው ወደ ስራ ይገባሉ፡፡
ለመሆኑ እነዚህ ህጎች ሲወጡ ምንን መሰረት አድርገው ነው? አንድ ህግ ከመውጣቱ በፊት ምን አይነት የአሰራር ሂደት መከተል አለበት?
የህግ አወጣጥ ሳይንስና በተግባር ያለው ልምድ ምን ያሳየናል? በሚለው ጉዳይ ዙሪያ የህግ ባለሙያዎችን ጠይቀናል፡፡
የህግ አወጣጥ የራሱ ሆነ ቅደም ተከል አለው ያሉን የአለም አቀፍ ህጎች ተንታኝና የህግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ ህግ የሚወጣው ማህበረሰቡን ለመጥቀም መሆን አለበት በተጨማሪም የጎደለ የአሰራር ክፍተትን በህግ ለማሟላት፣በህግ ማዕቀፍ ውስጥ መመራት ያለባቸው ጉዳዮች ሲኖሩ፣ህጉን ለማውጣት ባስፈለገበት ጉዳይ ዙሪያ ጥናት መደረግ አለበት እንዲሁም ለመፈፀም ይቻላል ወይ የሚለውም ታይቶ ነው ህግ መውጣት ያለበት ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ህግ አወጣጡ በራሱ ህግን የተከተለ መሆን አለበት፤ ይህንን ካልተከተለ በተለያዩ ምክንያቶች ፀድቆ ወደስራ ሊገባ ችላል ነገር ግን ህግ ስላለ ብቻ ልክ ነው ማለት አይደለም፤ህዝብን የሚጠቅም መሆን ሲገባው መቅጫ ሊሆን ይችላል ሲሉ የደብረታቦር ዩንቨርሲቲ የህግ መምህሩ አቶ መሳፍንት አላቸው ከታሪክ አጣቅሰው ነግረውናል፡፡
የህግ አወጣጥ ስርዓት እንዲህ ከሆነ በኢትዮጵያ እየወጡ ያሉ አዋጆች፣ደምቦችና መመሪያዎች እንዴት እየወጡ ነው? የህግ አወጣጥ ልማዳችን ምን ያሳየናል ያልናቸው ባለሙያዎቹ፤ ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ ያለው የህግ አወጣጥ ብዙ ጉድለት አለበት መጤን ያለባቸው ጉዳዮች አሉ የሚሉት ባለሙያዎቹ በተለይም የሚወጡ ህጎች የህዝቡን ጥቅም ማስጠበቅ አለባቸው የሚለውን በማንሳት ግለሰቦችን ወይም የተወሰኑ ብድኖችን ለመጥቀም ወይም ለመጉዳት የወጡ የሚመስሉ አዋጆች እንዳሉ አስተውለናል ይላሉ፡፡

አቶ ጥጋቡ ለማሳያነት የጠቀሱት በቅርቡ በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የፀደቀውና ታጥቀው ሲቀሳሰሱ የቆዩ የፖለቲካ ቡድኖች በህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት ተመዝግበው ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲመጡ የሚያስችለውን አዋጅ ከመሰረታዊው ህግ አወጣጥ ባፈነገጠ መልኩ ህውሃትን ለመጥቀም ሲባል እንዲሻሻል የተደረገ ነው በማለት ነው፡፡
ባለሙያው ይህንን ይበሉ እንጂ የህውሃት ቡድን አዋጁን እንደማቀበለውና ከመጥቀም ይልቅ እንደሚጎዳው ጠቅሷል፡፡
በነበረበት እንደሚቀጥል እንጂ ዳግም አልመዘገብም ሲል ከምርጫ ቦርድ ጋር የገባበት ውዝግብ አሁንም ድረስ አልተቋጨም፡፡
በሌላ በኩል በቅርቡ በህዝብ እንደራሴዎች ምክርቤት የፀደቀውና ብዙዎች ትችታቸውን ሲሰነዝሩበት የነበረው የመገናኛ ብዙሃ አዋጅ ሌላው ነው የሚሉት የህግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ፤ በቀደመው አዋጅ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የስራ አመራር ቦርድ አባላት ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ነፃና ገለልተኛ እንዲሆኑ ተደንግጎ የነበረው አሁን በተሻሻለው አዋጅ ተሸሮ የፖለቲካ ፓርቲ ተሳትፎ ያላቸው ግለሰቦች የስራ አመራር ቦርድ አባላት እንዲሆኑ ፈቅዷል፤ ይህ መሆኑ የገለልተንነት ጥያቄ ያስነሳል፤አዋጁ ሲፀድቅ ለፖለቲከኞች ታስቦ እንጂ ለሙያው ታስቦ አይደለም ባይ ናቸው ባለሙያው፡፡
ህግን ያልተከተሉ የህግ አወጣጥ ስርዓቶች ለአምባገነንነት በር ይከፍታል የሚሉት ባለሙያዎቹ አሁን እየታየ ባለው ልምድ የዳበረ የህግ አወጣጥ የለንም፤ ህጎች በዝርዝር በህዝቡ ውይይት ሳይደረግባቸው በችኮላ መፅደቅ የለባቸውም፤ ለዚሁ ነው የህግ የበላነት ማክበር ላይ ክፍተት የተፈጠረው፤የህግ አወጣጥ ሳይንስንመከተል ከዚህ መውጫመንገድ እንደሆነ አቶ ጥጋቡ ያነሳሉ፡፡
ህግ አውጪው አካል የሆነው ህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በበኩሉ ይፋዊ የህዝብ ውይይት አደርጋለሁ፤ በአዋጁ ዙሪያ የሚመለከታቸው ባለሙያዎችንና ሴክተር መስሪያ ቤቶችን ጋብዞ በማወያየት ግብረ መልስ እንዲሰጡት እንደሚያደርግ ሲናገር ይደመጣል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….. '
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
Comments