top of page

ሚያዝያ 24፣2016 - ሕብረት ባንክ የቅድመ ክፍያ ‘’ህብር ማስተር ካርድ’’ አገልግሎት ማስጀመሬን እወቁልኝ አለ

ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ኢትዮጵያዊያን በሌሎች የአለም ሀገራት የሚኖራቸውን ግብይት ምቹ በሆነ ሁኔታ እንዲያከናውኑ የሚያስችል፣ የፋይናንስ አካታችነትንና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማምጣት የሚያስችል የባንክ አገልግሎት መሆኑ ተነግሯል።


ሕብረት ባንክ ከማስተማር ካርድ እና ከፕሪሚየር ስዊች ሶሉሽን ግሩፕ ጋር በመተባበር ለአገልግሎት ክፍት ያደረገው የቅድመ ክፍያ ህብር ማስተር ካርድ አገልግሎት ዱዋል ኢንተርፌስ እንደሆነ ተነግሯል፡፡


ይህም ወደ ክፍያ ማሽኖች በማስገባት ወይም በማስጠጋት ብቻ አገልግሎት ማግኘት እንደሚቻል የሕብረት ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ከበደ ተናግረዋል።


ዛሬ በባንኩ ይፋ የተደረገው አገልግሎት የዲጂታል ፋይናንሺያል አካታችነትን የሚያሳይ ነው ያሉት አቶ መላኩ ‘’ደንበኞች የቅድመ ክፍያ ሕብር ማስተር ካርድ በመጠቀም ወደ ውጭ ሀገራት ጉዞ ሲያደርጉ በቀላሉ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ምቹ ነው’’ ብለዋል።

‘’ማስተር ካርድ በአፍሪካ የሚካሄደውን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ለማሳካት የሚደረገውን ጥረት ያሳያል’’ ያሉት የማስተር ካርድ በአፍሪካ ፕሬዝደንት ማርክ ኤሊየት ‘’ደህንነታቸው የተጠበቀና እና ምቹ የዲጅታል ክፍያ አማራጮችን በማስተዋወቅ ለሸማቾች እና ለነጋዴዎች ምቹ አማራSጮችን ለማቅረብ እና በአፍሪካ ዲጅታልን ለማስፋት በሚከወነው ተግባር ላይ እንደምንሳተፍ እወቁልን’’ ብለዋል።

የፕሪሚየር ስዊች ሶሉሽንስ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አመሃ ታደሰ፤ በአሁኑ ወቅት 46 ከመቶ የሚገኘውን የሀገሪቱን የፋይናንስ አካታችነት በ2025 ወደ 70 በመቶ ለማሳደግ ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል።


ህብረት ባንክ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያን የዲጂታል ገበያን ለማዘመን ሕብር ኢ-ኮሜርስ የተሰኘ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ተናግሯል።


ባንኩ የቅድመ ክፍያ ህብር ማስተር ካርድ አገልግሎቱን ከማስጀመር በተጨማሪ ዛሬ 25ተኛ ዓመቱን የብር ኢዮቤልዩ በዓሉን አክብሯል።


ፋሲካ ሙሉወርቅ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





bottom of page