top of page

ሚያዝያ  22፣2016 - የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ከማስተር ካርድ ጋር ተፈራረመ

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ወደ ውጭ ሀገር የሚጓዙ ደንበኞቹ  የውጭ ምንዛሪ  በቀላሉ በካርድ ማግኘት እንዲችሉ ከማስተር ካርድ ጋር ተፈራረመ።


የቅድመ ክፍያ ማስተር ካርድ አገልግሎት ወደ ውጭ ሀገር ለሚሄዱ ሰዎች በሚሄዱበት ሀገር የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ በካርዳቸው ላይ በውጭ ምንዛሬ የሚሞላለቸው እና ምንዛሬውን ደግሞ በብር የሚከፍሉበት ነው ተብሏል።


ተጓዦች በሄዱበት ሀገር ሁሉ መጠቀም የሚያስችል ነው ሲባል ሰምተናል።


በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ማስተር ካርድ እንደ ሀገር ያለውን የውጭ ምንዛሬ ጥሬ ገንዘብ ችግር በመቅረፍ ረገድ አስተዋጾ ያለውና የውጭ ጥሬ ገንዘብ ሸከምን የሚያስቀር ነው ተብሎለታል፡፡


የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ከዚህ በተጨማሪ  "ኮፕ ባንክ ኮሚኒቲ ፖስ " የተባለ አገልግሎት ከማስተር ካርድ ጋር በመሆን መጀመሩን ተናግሯል።

ይህ አገልገሎት ጥሬ ገንዘብን በማንቀሳቀስ የሚከናወነውን ተለምዷዊውን አሠራር በማስቀረት፣ የአርሶ አደሮችን መረጃ በኅብረት ሥራ ማህበራት በኩል በማቀናጀት፣ ኢንተርኔት በሌለበት ቦታ እንኳ አርሶ አደሮችንና ማህበራቱን የምርት ግብዓት፣ የግብርና ምርትና የፋይናንስ አገልግሎት በዲጂታል ስልት ማስተሳሰር  የሚያስችል ነው ተብሏል።


ይህም የገጠሩን ማህበረሰብ ለፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ እንዲሁም ዲጂታል ሽግግርን ማላመድን  ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው  ባንኩ አስረድቷል።


ባንኩ ባሁኑ ወቅት በመላው ሀገሪቱ 51,000 አርሶ አደሮች፣ 66 የኅብረት ሥራ ማህበራትና 7 ዩኒየኖችን በመመዝገብ ሥራው መጀመሩን ተናግሯል።


በዚህም 9200 ግብይቶችን በማከናወን 1.4 ሚሊዮን ዶላር  ምንዛሬ ያለው ገንዘብ በኅብረት ሥራ ማህበራትና በአርሶ አደሮች መሀከል ተንቀሳቅሷል ብሏል።


ባንኩ አገልግሎቱን በማስፋት የቡና፣ የገብስ፣ የስንዴና የዶሮ እርባታ የዕሴት ሰንሰለት ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅድ እንዳለው ጠቅሷል።


በዛሬው ዕለት ሥራ ላይ የዋሉት አገልግሎቶች ለ አምስት ዓመት የሚቆየውን በየኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ እና በማስተር ካርድ መሀከል በተደረገው ስትራቴጂካዊ ስምምነት ሊተገበሩ ከታቀዱት የመጀመሪያዎቹ ናቸው ተብሏል።


ንጋቱ ሙሉ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





bottom of page